አንጋፋው ጋዜጠኛ ጥላሁን በላይ በሕይወት ዘመናቸው ያሰባሰቧቸው መፅሃፍት ለኢዜአ በስጦታ ተበረከቱ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 10 ቀን 2013 (ኢዜአ) በቅርቡ በሞት የተለዩት አንጋፋው ጋዜጠኛ ጥላሁን በላይ በሕይወት ዘመናቸው ያሰባሰቧቸውን መፅሃፍት ይሰሩበት ለነበረው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) በስጦታ ተበረከተ።

ጋዜጠኛ ጥላሁን በላይ ከጀማሪ ሪፖርተርነት እስከ ከፍተኛ የስራ ክፍል ኃላፊነት በመስራት በኢዜአ እና በሌሎችም የመገናኛ በዙሃን አገልግለዋል።

አንጋፋው ጋዜጠኛ መጋቢት 16 ቀን 2013 ዓ.ም በተወለዱ በ77 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩ ሲሆን የነበሯቸው 3 ሺህ 500 መፅሃፍት ለተለያዩ የንባብ ማዕከላት፣ ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ለመገናኛ ብዙሃን በስጦታ ተበርክተዋል።

ስጦታውን ለኢዜአ ያስረከቡት የጋዜጠኛ ጥላሁን በላይ የእህት ልጅ አቶ ቴዎድሮስ ግዛው አጎታቸው

ለመፃህፍቶቻቸው ከምንም በላይ ፍቅር እንደነበራቸው ተናግረዋል።

"ጥላሁን በጣም የሚገርመኝ ምንም ጓደኛ የለውም፣ ትዳርም የለውም፣ ልጅም የለውም ሁለመናው መፅሃፍ  ነው ከመፅሃፍት ውጪ ምንም ሕይወት የለውም" ሲሉ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

ሰዎች መጽሐፍትን እንዲያነቡ ይመክሩ እንደነበርም አስታውሰዋል።

እንደ አቶ ቴዎድሮስ ገለጻ፤ ጋዜጠኛ ጥላሁን በቤታቸው የነበሯቸውን መፅሃፍት በሕይወት በነበሩ ጊዜም  ለተለያዩ ተቋማት የመስጠት ሃሳብ ነበራቸው።

በመሆኑም ይህንኑ ሃሳባቸውን ለመፈፀም ሊሰጧቸው ያስቡ ለነበሩት ተቋማት በማበርከት አንጋፋው ጋዜጠኛ እንዲታወሱ ለማድረግ ማሰባቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮዮጵያ ዜና አገልግሎት የህዝብ ግኑኙነትና ስትራቴጂ ዳይሬክተር አቶ ዮሐንስ ወንድራይድ "መፅሃፍቱ

የተቋሙን ጋዜጠኞች እውቀት ለማዳበር ያግዛሉ" ብለዋል።

የመፅሃፍት ስጦታ ከስጦታዎች ሁሉ የላቀ እንደሆነና ይህ ተግባር በተቋማትና በግለሰቦችም ሊለመድ የሚገባ መልካም ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።

አቶ ጥላሁን በላይ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት፣ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትና በኢትዮጵያ ሬዲዮ ዜና ፋይል በሪፖርተርነት፣ በዜና አዘጋጅነት፣ በአርታኢነትና በዜና ክፍል ሃላፊነት ከ40 ዓመት በላይ የዘለቀ የሙያ ልምድ የነበራቸው ጋዜጠኛ ነበሩ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም