ቀጥታ፡

የምርጫ ቁሳቁስ ስርጭት ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 10 ቀን 2013 (ኢዜአ) በመጪው ሰኞ ለሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ የድምፅ መስጫና ሌሎች ቁሳቁስ ማሸግና ማሰራጨት መጀመሩን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ገለፀ።

የቦርዱ የኮሙኒኬሽን አማካሪ ሶሊያና ሽመልስ በሰጡት መግለጫ በኦሮሚያ፣ በድሬዳዋ፣ በአፋር፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝና በጋምቤላ በሚገኙ የምርጫ ክልሎች የቁሳቁስ ስርጭት ተጀምሯል።

በአማራና በደቡብ ክልሎች የተወሰኑ የምርጫ ክልሎች የቁሳቁስ ስርጭቱ በቀጣዮቹ ቀናት እንደሚጠናቀቅ ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ምርጫ ክልሎች ለማዕከል ካላቸው ቅርበት አንፃር የቁሳቁስ ስርጭቱ በመጨረሻዎቹ ቀናት እንደሚከናወንም አስታውቀዋል።

በሌላ በኩል ለመራጮች ምዝገባ የተዘጋጁ ቦታዎች ለድምፅ መስጫና ቆጠራ ተግባራት ምቹ ባለመሆናቸው ቦርዱ አመቺ ቦታዎች እንዲዘጋጁ ጥያቄ ማቅረቡን ገልፀዋል።

በክልሎችና በገጠር ከተሞች የድምፅ አሰጣጥ ሂደትን የተመለከቱ የግንዛቤ መፍጠሪያ ትምህርቶች እየተሰጡ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ቦርዱ አካል ጉዳተኞችን ያማከሉ ስራዎችን እያከናወነ እንደሆነም ነው ወይዘሪት ሶሊያና ያስታወቁት።

ዛሬ በማህበራዊ ድረ-ገፆች አልፎ አልፎ የታዩ የምርጫ ቅስቀሳዎች ተገቢ ባለመሆናቸው መቆም እንዳለባቸውም የተናገሩት አማካሪዋ፤ ፓርቲዎችም ሆኑ የመገናኛ ብዙሃን የጥሞና ጊዜውን እንዲያከብሩ አሳስበዋል።

አገራዊው ምርጫ ሰኞ ሰኔ 14 ቀን 2013 ከማለዳው 12፡00 ሠዓት እስከ ምሽቱ 12፡00 ሠዓት ድረስ እንደሚካሄድም አስታውሰዋል።

በድምጽ መስጫው ቀን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጥንቃቄ እንዲደረግ ቦርዱ ግንዛቤ እየሰጠ መሆኑን ገልፀው፤ የጥንቃቄ እርምጃውን ሁሉም ተግባራዊ ሊያደርገው እንደሚገባ አስገንዝበዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም