ቀጥታ፡

ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ህብረተሰቡ የደርሻውን እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ

ባህር ዳር፤ ሰኔ 10/2013 (ኢዜአ) በመጪው ሰኞ የሚካሄደው ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ህብረተሰቡ ከፀጥታ ኃይሉ ጎን በመሆን የድርሻውን እንዲወጣ ፖሊስ ጥሪ ቀረበ።

የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር በሰላም ማስከበር ዙሪያ ዛሬ ማምሻውን መግለጫ ሰጥተዋል።

ኮሚሽነር ተኮላ አይፎክሩ በዚሁ መግለጫቸው እንዳስታወቁት፤ ምርጫው  ሰላማዊ ሆኖ  እንዲጠናቀቅ ፖሊስ አስፈላጊውን የቅድመ ዝግጅት ስራዎች በማጠናቀቅ የተቀናጀ ስምሪት አድርጓል።

በዚህም የፀጥታ ኃይሉ ከክልል እስከ ቀበሌ በሚገኙ  ሁሉም የምርጫ ክልሎችና ጣቢያዎች ስምሪት ተሰጥቶ አስፈላጊውን ጥበቃ እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

መራጩ ህዝብም ያለምንም የፀጥታ ስጋት ወጥቶ ይሆነኛል፣ ያስተዳድረኛል  ብሎ  ያመነበትን የፖለቲካ ፓርቲ እንዲመርጥም የፀጥት ኃይሉ አስፈላጊውን ሁሉ ጥበቃ ያደርጋል ብለዋል።

ቀደም ብሎ ከክልል እስከ ቀበሌ ለሚገኘው የፀጥታ ኃይል በምርጫ ወቅት ስለሚያከናውናቸው  የህግ ማስከበር ስራዎች አስፈላጊው ስልጠና መሰጠቱንም ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል።

የአካባቢውን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ የክልሉ የፀጥታ ኃይል ከፌደራል  ፖሊስ፣  ከመረጃና  ደህንነት፣ ከመከላከያና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት የተውጣጣ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ በቅንጅት እየሰራ እንደሚገኝም ኮሚሽነሩ አስረድተዋል።

 ህብረተሰብ በተለይም ወጣቱ ለሰላም መጠበቅ ከፀጥታ ኃይሉ ጎን  በመሆን  የአካባቢውን  ሰላም ነቅቶ በመጠበቅ የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅም ለህግ የበላይነት መከበር  ህዝቡ የራሱን አስተዋፅኦ እንዲያደርግም ኮሚሽነር ተኮላ አመልክተዋል።

ፖሊስ ከምርጫ በፊት፣ በምርጫው ዕለትና በኋላ ምን ማድረግ እንዳለበት ለአባላቱ አስፈላጊው ግንዛቤ መፈጠርን ጠቅሰው፤ ምርጫውን አስመልክቶ እስካሁን ያጋጠመ ነገር አለመኖሩንም ገልጸዋል።

በክልል ደረጃ የተቋቋመው ግብረ  ኃይል  በአንድ ማዕከል ሆኖ  ማንኛውንም ሊያጋጥም  የሚችል ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎችን ለመከላከል ሲሰሩ መቆየቱንና ይህም እስከ ምርጫው ማብቂያ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም