በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነ የህጻናት አትሌቲክስ ስልጠና ፓይለት ፕሮግራም ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነ የህጻናት አትሌቲክስ ስልጠና ፓይለት ፕሮግራም ተጀመረ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ሰኔ 10/2013 በኢትዮጵያ በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነ የህጻናት አትሌቲክስ ስልጠና የፓይለት ፕሮግራም ተጀመረ።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ እና የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፈዴሬሽኖች በትብብር የሚያከናውኑት ፕሮግራም ዛሬ በሁለት ትምህርት ቤቶች ተጀምሯል።
ፕሮግራሙ የሚሰጠው በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የሚገኘው ሰብስቴ ነጋሲና የካ ክፍለ ከተማ የሚገኘው የደጃች ወንድይራድ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ነው።
የስልጠና ፕሮግራሙ ዕድሜያቸው ከ7 እስከ 12 ዓመት የሆኑ ህጻናት የሚካፈሉበት መሆኑ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ቢልልኝ መቆያ ፕሮግራሙ በኢትዮጵያ በአይነቱ የመጀመሪያ መሆኑን ተናግረዋል።
ፌዴሬሽኑ ስልጠናው ውጤታማ እንዲሆን የትጥቅ፣ የቁሳቁስና የላብ መተኪያ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።
የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ቢኒያም ምሩጽ ፌዴሬሽኑ ከውድድር ይልቅ ለስልጠና ትኩረት እንደሚሰጥ ገልጸው ህጻናቱ ያገኙትን እድል በአግባቡ እንዲጠቀሙበት መክረዋል።
በሙከራ ፕሮግራሙ ውጤታማ የሚሆኑ ህጻናት በታዳጊዎች ፕሮጀክት ስልጠና የሚካተቱበት እድል እንደሚፈጠርላቸውም ጠቁመዋል።
ይህን መሰል ስልጠና በተለያዩ አገራት የሚተገበር እንደሆነና ለስኬቱም የዓለም አትሌቲክስ ድጋፍ እንደሚያደርግ ተገልጿል።
በኢትዮጵያ ለሚተገበረው ለዚሁ የህፃናት ስልጠናም የዓለም አትሌቲከስ ድጋፍ እንደሚያደረግ ተነግሯል።