ቀጥታ፡

ለሚዛን አማን አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ የመሰረተ ደንጋይ በመጣሉ መደሰታቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ገለጹ

ሚዛን፤ ሰኔ 10/2013 (ኢዜአ) ለረጅም ጊዜያት ቅሬታን ሲያሰነሳ የነበረው የሚዛን አማን የአውሮፕላን ማረፊያ ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ በመጣሉ መደሰታቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ   የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዋል።

ይህን ተከትሎ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች እንዳሉት፤ ለሚዛን አማን አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመሰረተ ድንጋይ ማሰቀመጣቸው ለህዝብ ያላቸውን ክብርና ፍቅር የሚገልጽ ነው።

ከነዋሪዎቹ  መካከል አቶ ነቢዩ አስፋው በሰጡት አስተያየት፤ የአውሮፕላን  ማረፊያ ሌላ ይቀየር ተብሎ እንደነበርና በዚሀም ቅሬታ አሳድሮባቸው እንደነበር አስታውሰዋል።

መንግስት በሰጠው ትኩረት  ቅሬታቸው መፍትሄ አግኝቶ በፈለጉበት ቦታ  የአውሮፕላን ማረፊያው ለመገንባት በጠቅላይ ሚኒስትሩ የመሰረተ ድንጋይ በመጣሉ መደሰታቸውን ገልጸዋል።

ግንባታው ቶሎ ተጀምሮ  እንዲጠናቀቅ የበኩላችንን ሚና እንወጣለን ብለዋል፡፡

ወጣት አምቦ አቸሮ በበኩሉ፤  የአካባቢውን ሀብት በአግባቡ ለዓለም አስተዋውቆ ተጠቃሚ ለመሆን የሚያስችል መሰረት ልማት በአካባቢው መምጣቱ ለተሻለ እድገት እንደሚያነቃቃ ተናግሯል፡፡

ሁሉም ልማት ተጀምሮ ሊጠናቀቅ የሚችለው ሀገር ሰላም ሲኖር በመሆኑ ሰላምን  በመጠበቅ በአካባቢው የሚሰሩ የልማት ተግባራት ከፍጻሜ እንዲደርሱ የድርሻውን እንደሚወጣ ገልጿል።

የአከባቢው አስተዳደርና ህዝቡ  የሚዛን አማን አውሮፕላን ማረፊያ እንዲገነባ   ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውን ያስታወሱት ደግሞ ሊቀጠበብት ቀለመ ወርቅ  ናቸው።

መንግስት በሰጠው ትኩረት ግንባታውን በተፈለገው ቦታ ለማካሄድ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የመሰረተ ድንጋይ መጣሉ  አስደሳች ነው ብለዋል።

ነዋሪዎቹ ለዶክተር አብይ አህመድ ያላቸውን ፍቅርና አክብሮት ገልጸዋል፡፡

የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው የአውሮፕላን  ማረፊያ ግንባታው የዘመናት የህዝቡን ጥያቄ እንደሚመልስና ለሀገሪቱ አኮኖሚያዊ  እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

ለግንባታው የድንጋይ በተጣለበት ስነ-ስርዓት የፌደራል፣ ክልልና አካባቢው  ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎች  የአውሮፕላን ማረፊያው ግንባታ ባለመካሄዱ  ለረጅም ጊዜያት ቅሬታ እንደነበራቸው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት  ቀደም ሲል ከስፍራው ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም