ቀጥታ፡

ኢትዮጵያዊያን ለምርጫው በሠላም መጠናቀቅ አገራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ

ሰኔ 10/2013 (ኢዜአ) አገራዊው ምርጫ ሠላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የምርጫው ተሳታፊዎችና መላው ኢትዮጵያዊያን አገራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጥሪ አቀረበ።

የጉባኤው የበላይ ጠባቂዎች በመጪው ሰኞ የሚካሄደውን ምርጫ አስመልክተው የሠላም ጥሪ በማቅረብ መግለጫ ሰጥተዋል።

የጉባኤው ጠቅላይ ጸሐፊ መስኡድ አደም ሁሉም ኢትዮጵያዊያን የምርጫውን ሠላማዊነት የማስጠበቅ  ኃላፊነት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

በተለይም ወጣቶች ግጭት ከሚቀሰቅሱና ከሚያስከትሉ ተግባራት በመራቅ የምርጫው ሂደት ሠላማዊ እንዲሆን አገራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አደራ ብለዋል።

የምርጫው ውጤት በህጋዊ አካል እስከሚገለፅ ድረስ ሁሉም በትዕግስት እንዲጠባበቅም በአጽንኦት ጠይቀዋል።

ምርጫውን የሚያስፈጽሙ አካላት፣ በምርጫ ወቅትና በድህረ- ምርጫ የሚከናወኑ ተግባራት ሁሉ ህግና ሥርዓትን በማክበርና በማስከበር ለሕዝብና ለአገር የገቡትን ቃል-ኪዳን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

የጸጥታና የደህንነት ተቋማት አመራሮችና ሠራተኞች ህግና ሥርዓትን በፍትሃዊነት ለመፈጸምና ለማስፈጸም የገቡትን ቃል ለአፍታም ሳይዘነጉና የገለልተኝነትን መርህ ሳይሸራርፉ እንዲያገለግሉም አደራ ብለዋል።

ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ምርጫ የሕዝብ ውሳኔ ሰጪነት ሚና በህግና በተግባር የሚረጋገጥበት ሂደት መሆኑን ባለመዘንጋት የሕዝቡ ፈቃድና ውሳኔ ምንም ይሁን ምን በማክበርና በማስከበር ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀርቦላቸዋል።

የኃይማኖት መሪዎችና አስተማሪዎች፣ ምዕመናን በዚህ ታሪካዊ ወቅት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡም የጉባኤው የበላይ ጠባቂዎች አሳስበዋል።

የመገናኛ ብዙኃን አመራሮች፣ ሠራተኞችና መረጃዎችን የሚያሰራጩ አካላትም በእውነት መርህ ላይ በመመርኮዝ የሚያሰራጩት መረጃ የህዝብና የአገርን ሠላም አደጋ ላይ የማይጥል እንደሆነ ሊያረጋግጡ ይገባል ብለዋል።

የየቤተ-እምነቶች አባቶችና የጉባኤው የበላይ ጠባቂዎች የምርጫው ሂደት ፍጹም ሠላማዊ እንዲሆን ሁሉም ታሪካዊ ኃላፊነቱን ይወጣ ዘንድ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ-ጳጳስና የጉባኤው የበላይ ጠባቂ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሱራፌል በመልእክታቸው

"በአጠቃላይ ምርጫው የሚደረገው ለሀገር ሠላም፣ ለሀገር አንድነት፣ ለሀገር ብልጽግና እንዲሁም ደግሞ ልማት መሆኑን ተገንዝበን ይህንን ሀላፊነት እንድንወጣ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በሁላችን ላይ እንዲወርድ እንድትጸልዩ አደራ እላለሁ።"

"ኢትዮጵያ አገራችን የሁላችንንም ትብብር ድጋፍ የምትሻ ሁላችንም ተሳስበን እንደ ሀገር ማስቀጠል፣ እንደ ሀገር መስራት ስለሚገባን ምርጫው በሠላም እንዲያልቅ ካለፈ በኋላ ካለ ምንም ሁከት የሚሸነፈውም የሚያሸንፈውም በጸጋ ተቀብሎ ምርጫው የሠላም እንዲሆን ለህዝበ ሙስሊሙ ይህንን ..አስተላልፋለሁ ድምጼን" ያሉት የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የቦርድ ምክትል ሰብሳቢና የተቀዳሚ ሐጂ ሙፍቲ ኢድሪስ ተወካይ ሼህ  መሃመድ ሲራጅ ናቸው።

የኢትዮጵያ ቃለ-ህይወት፣ የኢትዮጵያ መካነ-ኢየሱስ እና የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተክርስቲያናት ተወካዮችም የምርጫው ሂደት ሠላማዊ እንዲሆን ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ቃለ-ህይወት ቤተክርስቲያን ዋና ጸሐፊ ዶክተር ስሞኦን ሙላት በበኩላቸው "ይህ ምርጫ ሰኞ የሚደረግ ቢሆን በተለያየ ምክንያት ዘግይቶ ድምጽ የሚሰጡትም አካባቢዎች ቢሆኑ ምርጫው ሠላማዊ እንዲሆን ሁሉም ነገር በሠላም እንዲከናወን ጸሎታችንን አጥብቀን እንድንቀጥል አደራ እላለሁ" ብለዋል።

የኢትዮጵያ የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተክርስቲያን ፕሬዚዳንትና የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ ፓስተር ታደሰ አዱኛ "የሠላም ባለቤት የሆነው እግዚአብሄር ሠላም ሰጥቶናል፤ ያንን መንከባከብ መጠበቅ ከእያንዳንዱ ዜጋ ይጠበቃል"ብለዋል።

በሌላ በኩል ጉባኤው ሰሞኑን የአረብ ሊግ አባል አገራት ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ የምትገነባውን ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አስመልክቶ ያወጡትን መግለጫ ፍትሃዊ ያልሆነና የኢትዮጵያን ጥቅም የሚጎዳ መሆኑን ጠቅሰው እንደሚያወግዙት አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም