የግብፁ አል-አዝሃር ተቋም የአረብ ሀገራትን "ከግብፅና ከሱዳን ጎን ቁሙ" ማለቱ ከሃይማኖት የወጣና የሚወገዝ ተግባር ነው- ጠቅላይ ምክር ቤቱ - ኢዜአ አማርኛ
የግብፁ አል-አዝሃር ተቋም የአረብ ሀገራትን "ከግብፅና ከሱዳን ጎን ቁሙ" ማለቱ ከሃይማኖት የወጣና የሚወገዝ ተግባር ነው- ጠቅላይ ምክር ቤቱ
ሰኔ 10/2013 (ኢዜአ) የግብፁ አል- አዝሃር ኢስላማዊ ተቋም በህዳሴ ግድብ ዙሪያ የአረብ ሀገራትን "ከግብፅና ከሱዳን ጎን ቁሙ" በማለት ያስተላለፈው ጥሪ ሃይማኖታዊ መሰረት የሌለውና ፍፁም ተቀባይነት የሌለው መሆኑን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ገለጸ።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሃጂ ኡመር እንድሪስ፤ የግብፁ አል አዝሃር ኢስላማዊ ተቋም መሪ ሸህ አህመድ ጠይብ በዚሁ ዙሪያ ያስተላለፉትን መልእክት አውግዘዋል።
የተቋሙ መሪ ሸህ አህመድ ጠይብ የአረብ ሀገራትን "ከግብፅና ከሱዳን ጎን ቁሙ" በማለት ያስተላለፉት መልእክት ከሃይማኖት የወጣና የሚወገዝ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የምትከተለው ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ያማከለ አፍሪካዊ አስተሳሰብ ሆኖ ሳለ ግብፅና ሱዳን ግን እኛ ብቻ እንጠቀም ማለታቸው ተገቢነት የለውም ብለዋል ሃጂ ኡመር።
ኢትዮጵያ የአባይን ውሃ የመጠቀም መብት ማንም ሊከለክላት እንደማይችል ገልጸው የእስልምና አስተምህሮም የውሃ አጠቃቀምን አስመልክቶ ፍትሃዊ ፍርድ ያስቀምጣል ነው ያሉት፡፡
የኢትዮጵያ መንግስትና ሕዝብ የዓባይን ውሃ በእኩልነት እንጠቀም የሚል የሚያራምደውን አቋም ባልተገባ መንገድ መተርጎምም ሆነ ሃይማኖታዊ ጠርዝ እንዲኖረው መሞከር ሃይማኖታዊ መሰረት የለውም፤ ፍፁም ተቀባይነትም አያገኝም ነው ያሉት።
በሌላ መልኩ በቀጣይ ሰኞ የሚካሄደው ምርጫ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሁሉም ህብረተሰብ ለሰላም ቅድሚያ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።
ምርጫው በሰላም ተጀምሮ በሰላም እንዲጠናቀቅ ወላጆች ልጆች አስተማሪዎችም ሆኑ የፖለቲካ አመራሮች ለሰላም ቅድሚያ ሰጥተው እንዲሰሩም ጥሪ አቅርበዋል፡፡