የአፍሪካ የሰብዓዊና የሰዎች መብት ኮሚሽን በትግራይ ያለውን ሁኔታ በተመለከተ ለብቻው "መርማሪ ኮሚሽን "ማቋቋሙን የኢትዮጵያ መንግስት አይቀበለውም--የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ የሰብዓዊና የሰዎች መብት ኮሚሽን በትግራይ ያለውን ሁኔታ በተመለከተ ለብቻው "መርማሪ ኮሚሽን "ማቋቋሙን የኢትዮጵያ መንግስት አይቀበለውም--የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
ሰኔ 10/2013 (ኢዜአ) የአፍሪካ የሰብዓዊና የሰዎች መብት ኮሚሽን በትግራይ ያለውን ሁኔታ በተመለከተ ለብቻው "መርማሪ ኮሚሽን "ማቋቋሙን የኢትዮጵያ መንግስት እንደማይቀበል አስታወቀ፡፡
ኮሚሽኑ "መርማሪ ኮሚሽን ሟቋቋሙን" በተመለከተ ያስተላለፈው መልዕክት የኢትዮጵያ መንግስትን ጥሪ ወደ ኋላ የተወና ህጋዊ መሰረት የሌለው መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይህንኑ አስመለክቶ ባወጣው መግለጫ የአፍሪካ የሰብዓዊና የሰዎች መብት ኮሚሽን በትግራይ ክልል የተከናወነውን ህግ የማስከበር ዘመቻ ተከትሎ ደረሰ የተባለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለመመርመር ያደረገውን ዝግጅት ተገቢ አለመሆኑን አመላክቷል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት የካቲት 2 ቀን 2013 ዓ.ም የአፍሪካ አገራት መሪዎች በተሰባሰቡበት በተደረገው የአፍሪካ የሰላምና ደህንነት ካውንስል ጉባኤ ላይ በትግራይ የተከናወነውን ህግ የማስከበር ዘመቻ ተከትሎ ኮሚሽኑ በክልሉ የደረሰውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት በተመለከተ በሚያደርገው ምርመራ ላይ በጋራ ለመሳተፍ ያለውን ዝግጁነት በይፋ መግለጹን መግለጫው አመላክቷል፡፡
ይህንኑ ተግባራዊ ለማድረግ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጉዳዩን በተመለከተ የህብረቱ የሰላምና ደህንነት ካውንስል የፖለቲካ ምክረ ሃሳብ የሚሰጥበትን አግባብ በተመለከተ ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ጋር የካቲት 4 ቀን 2013 ዓ.ም ተወያይተዋል፡፡
በዚሁ መሰረት የህብረቱ ሊቀመንበር የኢትዮጵያን ተነሳሽነት በማድነቅ በህብረቱ ስምምነት በተቋቋመ አካል ጉዳዩ እንዲታይ መደረጉ ያለውን ጠቀሜታ አስረግጠው መናገራቸውን በእለቱ ባወጡት መግለጫ መግለፃቸው ይታወሳል፡፡
በተጨማሪ የአፍሪካ የሰብዓዊና የሰዎች መብት ኮሚሽን ምርመራውን በጋራ ለማከናወን የቀረበውን ምክረ ሃሳብ መቀበሉን የሚገልጽ ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚኒሰትር አብይ አህመድ መላኩንም መግለጫው ጠቁሟል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስትም ለተላከለት ደብዳቤ በሰጠው ምላሽ በምርመራው ላይ ለመሳተፍ ፍላጎት እንዳለውና ይህንኑ የሚከታተል ቃል አቀባይ ተቋም እንደሚያቋቁም አረጋግጧል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአፍሪካ የሰብዓዊና የሰዎች መብት ኮሚሽን በተናጠል “ምርመራ የሚያደርግ ኮሚሽን ” ማቋቋሙን ይፋ ማድረጉ አሳዛኝ ተግባር መሆኑን ሚኒስቴሩ በመግለጫው አመላክቷል፡፡
ተግባሩ የመንግስትን ጥሪ ወደ ጎን የገፋና ህጋዊ መሰረት የሌለው መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ያም ቢሆን የኢትዮጵያ መንግስት በጋራ የሚደረገውን ምርመራ የተሳካ ለማድረግ አስፈላጊውን መደላደል ለማሟላት በቀና እምነት የሚጠበቅበትን ሁሉ ለማከናወን ዝግጁ መሆኑን አረጋግጧል፡፡
ኮሚሽኑ አቋቋምኩት ያለውን “መርማሪ ኮሚሽን ” በተመለከተ በተናጠል ያወጣው መግለጫ የትብብር መንፈስን ወደ ኋላ የተወና የኢትዮጵያ መንግስት የተጠቀሰውን ምርመራ ለማከናወን የያዘውን ጥረት የሚደግፍ መደላደል ለመፍጠር የጀመረውን ጥረት ያላገነዘበ መሆኑን ገልጿል፡፡
ተግባሩ ከአፍሪካ የሰብአዊና የሰዎች መብት ቻርተር ጋር የሚጣረስና ኮሚሽኑ ራሱ የሚከተለውን የማስፈጸሚያ ደንብ የሚጻረር መሆኑ በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡
የአፍሪካ የሰብዓዊና የሰዎች መብት ኮሚሽን ራሱ የአፍሪካ ህብረት ተቋም በመሆኑ ከህብረቱ አባል አጋራት ጋር ገንቢ የሆነና መመሪያን መሰረት ያደረገ ግንኙነት ሊኖረው ይገባል ተብሏል፡፡
ይህንኑ ተገቢ ያልሆነና ለማንም የማይጠቅም አካሄድ ወደ ጎን በመተው ተቀባይነት ያገኘውን የጋራ ምርመራ ለማድረግ የሚረዳ ትብብር ለማድረግ የሚያስችሉ እድሎች መኖራቸውን ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡
ኮሚሽኑ የወሰደው ጠቃሚ ያልሆነ ተግባር የአህጉሪቱን የሰብዓዊና የሰዎችን መብት ጥበቃ ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት ወደ ፊት የማያሻግርና ጥበቃውን እውን የማያደርግ ከመሆኑ በላይ በአባል አገራት መካከል ያለውን የጋራ መተማመን ከግንዛቤ ያልከተተ ነው ይላል መግለጫው፡፡
ኮሚሽኑ በተሳሳተ መንገድ ጉዞውን ለመቀጠል መምረጡ የተቋቋመበትን ዓላማ በእጅጉ የሚጣረስ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በያዘው አቋም ለመቀጠል ዝግጁ መሆኑን በማስታወቅ ኮሚሽኑ እየሄደበት ያለውንና የኢትዮጵያ መንግስት እውቅና ያልሰጠውን አካሄድ በፍጥነት እንዲያቆም ጠይቋል፡፡
ከዚህ ይልቅ ኮሚሽኑ በኢትዮጵያ ከሚገኙ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተጋገዝ የተቀመጠውን የምርመራ ሂደት ማሳለጥ ይጠበቅበታል ሲል መግለጫው አመላክቷል፡፡