በአማራ ክልል ከ70 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች ድጋፍ ተደርጓል - ቀይ መስቀል ማህበር - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል ከ70 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች ድጋፍ ተደርጓል - ቀይ መስቀል ማህበር
ጎንደር ሰኔ 10/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በአማራ ክልል በተለያዩ ዞኖች ተከስቶ በነበረ የጸጥታ ችግር ለተፈናቀሉ ከ70 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች ሰብአዊ ድጋፎችን መስጠቱን አስታወቀ።
ማህበሩ በክልሉ ስለሚሰጠው የሰብአዊ አገልግሎት ድጋፍ ከተለያዩ ዞኖች ለተውጣጡ መንግስታዊ አካላትና የማህበረሰብ ክፍሎች ዛሬ በጎንደር ከተማ የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይት አካሂዷል፡፡
በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ሃላፊ አቶ ሻምበል ዋለ በወቅቱ እንደገለጹት ድጋፉ የተደረገው ባላፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ ነው።
በክልሉ በተለያዩ ዞኖች ተከስቶ በነበረ የጸጥታ ችግር ተፈናቅለው በመጠለያ ለሚገኙ ከ70 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች ግምቱ 25 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የሰብአዊ ድጋፍ ተሰጥቷል፡፡
ለተፈናቃዮች ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችን ጨምሮ የአምቡላንስና የመጀመሪ ደረጃ የህክምና እርዳታ አገልግሎት መሰጠቱን ተናግረዋል።
ለእናቶችና ህጻናት ደግሞ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ድጋፍ መደረጉን ሃላፊው አስታውቀዋል፡፡
የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ያያለም ፈንታሁን በበኩላቸው የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በትህነግ ኢሰብአዊ እርምጃ ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ዞኑ ለመጡ የመከላከያ ሰራዊት አባላት የህክምናና የምግብ ድጋፍ በማድረግ ሰብአዊ ድጋፍ መስጠቱን ገልጸዋል፡፡
ማህበሩ ከትግራይ ክልል እንዲሁም ከሱዳን ተፈናቅለው ለመጡ ወገኖችም የአልባሳት የምግብና የመጠለያ ድጋፍ በማበርከት ዜጎችን የመታደግ ሰፊ የሰብአዊ አገልግሎት ስራ ማከናወኑን ተናግረዋል፡፡