በምርጫው ድምጽ በመስጠት ሰራተኞች ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን በአግባቡ ሊጠቀሙበት ይገባል- ኮንፌዴሬሽኑ - ኢዜአ አማርኛ
በምርጫው ድምጽ በመስጠት ሰራተኞች ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን በአግባቡ ሊጠቀሙበት ይገባል- ኮንፌዴሬሽኑ
አዲስ አበባ ሰኔ 10/2013 (ኢዜአ) "በምርጫው መብታቸውን ያስከብርልኛል ለሚሉት ወገን ድምጽ በመስጠት ሰራተኞች ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን በአግባቡ ሊጠቀሙበት ይገባል" ሲል የኢትዮጵያ አሰሪ ፌዴሬሽኖች ኮንፌዴሬሽን አስታወቀ።
አሰሪዎች ለሠራተኞች በምርጫው እለት ድምጻቸውን እንዲሰጡ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉም ተጠይቋል።
የዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ የድምፅ መስጫ እለት የፊታችን ሰኞ እንደሚካሄድ ይታወቃል።
የኢትዮጵያ አሰሪ ፌዴሬሽኖች ኮንፌዴሬሽን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ኢንጂነር ጌታሁን ሁሴን፤ ምርጫው በተለየም ለሰራተኞች ትልቅ ትርጉም እንዳለው ይናገራሉ።
አሰሪዎችና ሠራተኞችም ምርጫው ለኢትዮጵያ ሰላም፣ እድገትና ልማት ተስፋ የሰነቀ መሆኑን በመረዳት ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ለመጠቀም መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ መሥራትና ሀብት ማፍራት ሕገ-መንግሥታዊ መብቱ እንደሆነና ይህን መብት ለማስጠበቅ ሰላምና መረጋጋት መኖር እንዳለበት ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶችም ለሠራተኞች ምቹ የሆነ የሥራ ሁኔታ መፍጠር ኃላፊነት መኖሩን ጠቅሰዋል።
ሠራተኞም በምርጫው ድምጽ ሲሰጡ መብታቸውንና ጥቅማቸውን ያስከብርልኛል ብለው ለሚያስቡት አካል ድምጻቸውን በመስጠት ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን በአግባቡ መጠቀም አለባቸው ነው ያሉት ኢንጂነር ጌታሁን።
ሠራተኛው በምርጫው ተሳትፎ ሳያደርግ "ዝም ብሎ በመመልከት" መብቴ ይከበራል ብሎ መጠበቅ እንደሌለበትም ተናግረዋል።
አሰሪዎች በተለይም የግል ድርጅቶች ቀጥረው የሚያሰሯቸውን ሠራተኞች በድምጽ መስጫው ዕለት ድምጽ እንዲሰጡ አስፈላጊውን ትብብር ሊያደርጉላቸው እንደሚገባም አመልክተዋል።
ሰራተኞችም መንግሥት ባስተላለፈው መመሪያ መሰረት ከምርጫው በኋላ በሚመጣው ቅዳሜ በሥራ ገበታቸው ላይ በመገኘት አገልግሎት መስጠት አለባቸው ብለዋል።
አሰሪና ሠራተኞች ከአጠቃላይ ምርጫው በተጨማሪ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ላይ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ አሰሪ ፌዴሬሽኖች ኮንፌዴሬሽን በመስከረም ወር 2013 ዓ.ም የኢትዮጵያ አሰሪዎች ኮንፌዴሬሽንና የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ አሰሪዎች ኮንፌዴሬሽን በመዋሀድ የፈጠሩት ተቋም ነው።
በ6ኛው አጠቃላይ ምርጫ ከ37 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ መራጮች መመዝገባቸውን ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በጸጥታ ችግር፣ የድምጽ መስጫ ወረቀት ሕትመት ችግር ባለባቸውና የፍርድ ቤት ውሳኔ በተሰጠባቸው የምርጫ ክልሎች ጳጉሜን 1 ቀን 2013 ዓ.ም ድምጽ እንዲሰጥ ቦርዱ ወስኗል።
በተጨማሪም የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልልነት ሕዝበ ውሳኔ በተመሳሳይ ጳጉሜን 1 ቀን 2013 ዓ.ም ይካሄዳል።