የሞጆ ደረቅ ወደብ የሎጅስቲክ አገልግሎት ማዕከል ማስፋፊያ ግንባታ ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የሞጆ ደረቅ ወደብ የሎጅስቲክ አገልግሎት ማዕከል ማስፋፊያ ግንባታ ተጀመረ

አዳማ ፤ ሰኔ 10/2013 (ኢዜአ) በሀገሪቱ ቀዳሚ የሆነውን የሞጆ ደረቅ ወደብ የሎጀስቲክ አገልግሎት ማዕከል በ150 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወጪ ለማስፋፋት ዛሬ የግንባታው ስራ ተጀመረ።
የማስፋፊያ ግንባታውን ያስጀመሩት የትራንስፖርት ሚኒስትር ዳግማዊት ሞገስ ናቸው።
ሚንስትሯ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት፤ የማስፋፊያ ግንባታው ማዕከሉ አገልግሎቱን የሚያፋጥን ከመሆኑም ባለፈ ለኢትዮ-ጂቡቲ የኢኮኖሚ ቀጠናዊ ንግድ መቀላጠፍ የላቀ ሚና ይኖረዋል።
የሞጆ ደረቅ ወደብ የሎጅስቲክ አገልግሎት ማዕከል ሙሉ በሙሉ ታዳሽ ሃይል የሚጠቀምና የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ፕሮጀክት አካል መሆኑን አስታውቀዋል።
ደረቅ ወደቡን ሁለገብ የሎጅስቲክ አገልግሎት ማዕከል በማድረግ ሀገራዊ፣ ቀጠናዊና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆን የሚመቻች መሆኑን ሚኒስትሯ ገልጸዋል።
ወደቡ ሀገሪቱ ቀጣይ የልማትና ዕድገት ጉዞን መሸከም የሚችል ቴክኖሎጂ እንደሚሟላለት አስረድተዋል።
ሁለገብ የሞጆ ደረቅ ወደብ የሎጅስቲክ አገልግሎት ማዕከልን ለማስፋፋት የተጀመረው ግንባታ ከዓለም ባንክ በብድር በተገኘ 150 ሚሊዮን ዶላር መሆኑን አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያን የወጪና የገቢ ንግድ ከማሳለጥ ባለፈ ለበርካታ ወጣቶች የስራ ዕድል የሚፈጥር ነው ያሉት ደግሞ በዓለም ባንክ የኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን ቀጠናዊ ዳይሬክተር ሚስተር ዑስማኔ ዳዮን ናቸው።
በ4 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር የሚከናወነው የወደቡ የሎጀስቲክ አገልግሎት ማዕከል የመልቲ ሞዳልና የተሟላ የንግድ ስርዓት እንዲረጋገጥ የሚያስችል ነው ብለዋል።
በተጨማሪም የገቢ ሸቀጦችን ከጂቡቲ ወደብ በፍጥነት ለማንሳት እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
የሞጆ ሀዋሳ የፍጥነት መንገድ መገንባት የግብርና ምርቶች ፈጥነው ወደ ደረቅ ወደቡ እንዲጓጓዙ የሚያስችልና ለበርካታ ወጣቶች የስራ ዕድል የሚፈጠር መሆኑንም ገልጸዋል።
የዓለም ባንክ የኢትዮጵያን ልማት ለመደገፍ የጀመረውን እገዛ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የማሪታይም ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን አበራ በበኩላቸው ፤ የሞጆ ደረቅ ወደብ የሎጅስቲክ አገልግሎት ማዕከል በሀገራችን ቀዳሚ ነው ብለዋል።
በማስፋፊያው ግንባታ በተለይ ስድስት ዘመናዊ የማቀዝቀዣ መጋዘኖች፣ መንገዶች፣ የከባድ ማሽነሪዎች እንቅስቃሴ፣ የውሃና ፍሳሽ ማስወገጃ፣ የእሳት አደጋ መከላከያና የንፅህና መጠበቂያ መሰረተ ልማቶች እንደሚያካትት አስረድተዋል።
የኤሌክትሮኒክስና ሌሎች ህንፃዎች ጭምር የሚያካትት የማስፋፊያ ግንባታ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል።