በከተሞች እየጨመረ የመጣው የአየር ብክለት በኢኮኖሚና ጤና ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ተባብሷል- ኮሚሽኑ - ኢዜአ አማርኛ
በከተሞች እየጨመረ የመጣው የአየር ብክለት በኢኮኖሚና ጤና ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ተባብሷል- ኮሚሽኑ
አዲስ አበባ ሰኔ 10/2013 (ኢዜአ) በከተሞች እየጨመረ የመጣው የአየር ብክለት በኢኮኖሚና ጤና ላይ የሚያስከትለው ጉዳት እየተባባሰ መሆኑን የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን አስታወቀ።
የአየር ጥራት፣ የአጭር ጊዜ የበካይ ጋዞች ቅነሳና የተቋማት የጋራ ዕቅድ ማጣጣሚያን አስመልክቶ ኮሚሽኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።
የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ፍሬነሽ መኩሪያ፤ ባደረጉት ንግግር በተለይ በከተሞች እየጨመረ የመጣው የአየር ብክለት በኢኮኖሚና ጤና ላይ የሚያስከትለው ጉዳትን አባብሶታል።
በተለይ የሃይል አጠቃቀም፣ የተሽከርካሪዎች ቁጥርና የነዳጅ ፍጆታ መጨመር፣ የግንባታ ስራዎች፣ ኢንዱስትሪዎችና ከተሞች መስፋፋትና በዜጎች የኑሮ ዘይቤ ለውጥ ሳቢያ የአየር ብክለት መጨመረ የአጭር ጊዜ አየር በካይ ቅንጣቶችና ጋዞች ክምችት እንዲጨምር አድርጓል ብለዋል።
የአየር ብክለትን የመለካትና የመቆጣጠር እንዲሁም የአካባቢ ክብካቤ ስርዓቶች በአግባቡ ባለመተግባራቸው ችግሩ ተባብሶ መቀጠሉን አብራርተዋል።
በአገሪቱ በየዓመቱ ከሚሞቱ ሰዎች መካከል14 በመቶው በአየት ብከለት ሳቢያ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በአየር በብክለቱ ከሚሞቱ ሰዎች መካከል አብዛኞቹ በቤት ውስጥ የአየር ብከለት ነው።
በኢትዮጵያ ችግሩን ለመፍታት በ2030 ዘላቂ የልማት ግቦች ውስጥ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የተለያዩ ተግባራት በማከናወን ላይ መሆናቸውን ምክትል ኮሚሽነሯ ገልጸዋል።
ባለፉት አምስት ዓመት የከተሞች የአየር ጥራት ማሻሻያ እቅድ ተነድፎ ወደ ሰራ መገባቱን አስታውሰው በትግበራው ግን የሚፈለገው ውጤት አለመገኘቱን ጠቁመዋል።
በተለይ ብክለትን የመለካትና የመቆጣጣር እንዲሁም የአካባቢን ክብካቤ ስርዓቶች በአግባቡ ያለመተግበር ዋነኛ ችግሮች መሆናቸውን አንስተዋል።
የዛሬው የምክክር መድረክም የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት ተቋማት የራሳቸውን ሃላፊነት እንዲወጡ ለማስቻል ነው ብለዋል።
በተለይ የአየር በካይ ቁሶች እንዲቀንሱ በነዳጅና የተሽከርካሪ አጠቃቀም፣ በጤና መረጃ በግንባታና የቆሻሻ አያያዝ ላይ መሰረታዊ ለውጦች ማምጣት እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአረንጓዴ ልማት አሻራዎች በአገሪቱ ለአየር ብከለት ትልቅ ተስፋ ጥሏል ነው ያሉት።
ይህ ስራ እውን እንዲሆን ሁሉም የድርሻውን መወጣት ይጠበቅበታል በለዋል።
በጤና ሚኒስቴር የሃይጂንና የአካባቢ ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ ሸረፈዲን ዩያ እንዳሉት በአየር በብክለት ሳቢያ በተለይ እናቶችና ህጻናት በከፍተኛ ሁኔታ ተጎጂዎች እየሆኑ ነው።
በቂ አየር በማይዘዋወርበት ቤት ውስጥ ምግብ በማብሰል ሂደት ልጆቻቸውም ስለሚኖሩ ለችግሩ በስፋት ይጋለጣሉ ብለዋል።
በመሆኑም ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ በመምጣቱ የፖሊሰና የተቋማት የተቀናጀ ትግበራ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።