ቀጥታ፡

የጃፓን መንግስት ለዓለም አቀፍ ሠላም ማስከበር ማሠልጠኛ ተቋም ድጋፍ አደረገ

ሰኔ 10/2013(ኢዜአ) የጃፓን መንግሥት ለዓለም አቀፍ የሠላም ማስከበር ማሠልጠኛ ተቋም የ850 ሺህ ዶላር ድጋፍ አደረገ።

የገንዘብ ድጋፉ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት መርኃ ግብር በኩል የሚያልፍ ሲሆን፤ ለማሠልጠኛ ተቋሙ አቅም ግንባታ እንደሚውል ተገልጿል።

በመከላከያ ሚኒስቴር የዓለም አቀፉ የሠላም ማስከበር ማሰልጠኛ ተቋም ኃላፊ ብርጋዴር ጄኔራል ሰብስቤ ዱባና የመንግሥታቱ ድርጅት የልማት መርኃ ግብር ምክትል የኢትዮጵያ ተወካይ ሴሌኦፋስ ቶሮሪ የድጋፍ ሥምምነቱን ተፈራርመዋል።

ብርጋዴር ጄኔራል ሰብስቤ ድጋፉ በቀዳሚነት ለተቋሙና በውስጡ ለሚገኘው የሰው ኃይል አቅም ግንባታ እንደሚውል ተናግረዋል።

ተቋሙ የሠላም ማስከበር ተልዕኮውን ውጤታማ ማድረግ የሚያስችሉ ሥልጠናዎች ለመስጠትና የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ድጋፉ ትልቅ አቅም ይሆናል ነው ያሉት።

በተጨማሪም በዓለም አቀፍ የሠላም ማስከበር ተልዕኮ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለመሙላትና ቀጣናዊ የተጠባባቂ ኃይልን ለመደገፍ እንደሚያግዝም ገልጸዋል።

የጃፓን መንግሥት ተመሳሳይ የሥልጠና መርሃ ግብር ድጋፎችን እያደረገ መሆኑን አስታውሰው፤ ይህ "አጋርነት ሊቀጥል ይገባል" ብለዋል።

የተመድ የልማት መርኃ ግብር ምክትል የኢትዮጵያ ተወካይ ሴሌኦፋስ ቶሮሪ በበኩላቸው ድጋፉ ተቋሙ ተልዕኮውን እንዲያሳካ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቁመዋል።

የተደረገው ድጋፍ ጃፓን ለዓለም በተለይም ለአፍሪካ ሠላምና ደኅንነት ጉዳዮች ያላትን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ኢቶ ታካኮ በበኩላቸው፤ አገራቸው የአፍሪካን በተለይም የምስራቅ አፍሪካን ሠላምና ደኅንነት ለማስከበር በትኩረት እንደምትሰራ ገልጸዋል።

ይህንን ለማድረግና የሠላም ተልዕኮውን ለማጠናከር ጃፓን ከመከላከያ ዓለም አቀፍ የሠላም ማስከበር ማሠልጠኛ ተቋም ጋር በጋራ እየሰራች መሆኗን ጠቅሰዋል።

ጃፓን ከማሠልጠኛ ተቋሙ ጋር ያላትን አጋርነት አጠናክራ እንደምትቀጥልም አረጋግጠዋል።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም