ቀጥታ፡

"ለመልካም ፉክክራችሁ ምስጋናዬ ብዙ ነው" -- ብርቱካን ሚደቅሳ

ሰኔ 10/2013 (አዜአ) የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ "ለመልካም ፉክክራችሁ ምስጋናዬ ብዙ ነው " ሲሉ ለተፎካካሪ ፓርቲዎች ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የፊታችን ሰኞ በሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ የሚሳተፉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምረጡኝ ዘመቻ ትላንት መጠናቀቁን የምርጫ ቦርድ አስታውቋል፡፡

የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ፤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት "ጥላቻን በውስጣችሁ ይዛችሁ አልተወዳደራችሁም፤ በአደባባይ ዘለፈኝ፤ ስሜን አጠፋ አልተባባላችሁም ወይም ይህን ስትሉ እኔ አገልጋያችሁ አልሰማሁም" ብለዋል።

"እንደ አምና ካችአምናው ይቅርታ ካልጠየቀኝ ሞቼ እገኛለሁ፤ ከሱ ጋር ሁለተኛ አልቆምም" በማለት የተናገረ አለመኖሩንም ጠቅሰዋል።

"ለመልካም ፉክክራችሁ ምስጋናዬ ብዙ ነው" ያሉት የቦርዱ ሰብሳቢ ቀጣዮቹ የፅሞና ቀናት የበጎነት እና የመልካምነት ጊዜ እንዲሆንላችሁ "የልቤን መቃተት ለካፍላችሁ ወደድኩ" ብለዋል በመልእክታቸው። 

ለሞከርናት ትንሽ የጋራ ሙከራ የጎን ውጋት ሆናችሁ ለከረማችሁትም ጭምር ምስጋናዬ ይድረሳችሁ ብለዋል፡፡

የምርጫ ቅስቀሳ መጠናቀቁን በተመለከተ የቦርድ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች አማካሪ ሶልያና ሽመልስ ቀሪዎቹ አራት ቀናት የምርጫ ቅስቅሳዎች የማይኬዱባቸው፣ ማኅበረሰቡ ስለ ድምፅ አሰጣጥ ብቻ መረጃ የሚያገኝበትና ማንን መምረጥ እንዳለበት ለማሰብ የጽሞና ወይም የጸጥታ ጊዜ የሚያገኝበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎችና ደጋፊዎቻቸው ትናንትና የመጨረሻ ቅሰቀሳቸውን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ማካሄዳቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

ቦርዱ የጥሞና ወቅት በቅድመ የምርጫ ዑደት ውስጥ የሚገኝና በኢትዮጵያ የምርጫ ዑደት መመሪያ መሠረት ምርጫ ከመደረጉ በፊት ያሉትን አራት ቀናት የሚያካትት መሆኑን በተቋሙ ድረ ገጽ ላይ አስታውቋል፡፡ 

በጥሞና ወቅት የተለያዩ ባለድርሻ አካላት፤ ማለትም የፖለቲካ ፓርቲዎችና የመገናኛ ብዙሀን ተቋማት ሊተገብሯቸው የሚገቡ ሀላፊነቶች መኖራቸው እንዲሁ፡፡

በዚህም የፖለቲካ ፓርቲ እጩዎችና ደጋፊዎቻቸው ቦርዱ በሚያወጣው መመሪያ መሠረት የሚያካሂዱት የምርጫ ውድድር እንቅስቃሴ ድምጽ መስጠት ከመጀመሩ ከአራት ቀን በፊት መጠናቀቅ እንዳለበትና ፣ ምርጫው አራት ቀን ሲቀረው ማንኛውም አይነት የምርጫ ቅስቀሳ ማድረግ እንደማይፈቀድላቸው ጠቅሷል፡፡ 

በተጨማሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ጉዳዮች ዙሪያ አስተያየት ከመስጠት እንዲሁም ቃለ-መጠይቆችን ማድረግ አይፈቀድላቸውም ተብሏል፡፡

ብሄራዊ የምርጫ ቦርድ የሚያወጣቸውንም መመሪዎች ሊፈጽሙ እንደሚገባ አመላክቷል፡፡

የመገናኛ ብዙሀን ተቋማት በበኩላቸው በጥሞና ወቅት ማንኛውንም ምርጫ ተኮር እንቅስቃሴዎችን ማሰራጨት አይፈቀድላቸውም ተብሏል፡፡ 

በተጨማሪም የፓለቲካ ፓርቲ እጩዎችን አግኝተው ቃለ መጠይቆችን መስራት አይፈቀድላቸውም፡፡

የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ከብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የሚወጡ መረጃዎችን የማስተጋባት ሃላፊነት ሲኖርባቸው ከዚህ ውጪ በመመሪያዎች ላይ ያልተደነገጉ ተግባራትን እንዲፈጽሙ አይፈቀድላቸውም ሲል ምርጫ ቦርድ አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ዶክተር ራሄል ባፌ፣ የምርጫው ሂደት ለዚህ ደረጃ መብቃቱን ገልጸው ተስፋና ሥጋቱ ግን ከምርጫውም በኋላ የሚቀጥል በመሆኑ ቀሪ ሥራዎች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም