የውጭ ጫናን ለመቋቋም የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድነቱ ፀንቶ መቆም እንዳለበት የኃይማኖት አባቶች አሳሰቡ - ኢዜአ አማርኛ
የውጭ ጫናን ለመቋቋም የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድነቱ ፀንቶ መቆም እንዳለበት የኃይማኖት አባቶች አሳሰቡ
ባህር ዳር ፤ ሰኔ 10/2013(ኢዜአ) ሀገሪቱን ለማዳከም እየተሞከረ ያለው የውጭ ጫና ለመቋቋም የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድነቱ ፀንቶ መቆም እንዳለበት የኃይማኖት አባቶች አሳሰቡ።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የኃይማኖት አባቶች እንዳሉት፤ ህዝቡ ሃገር እንዳቀኑት አባቶቹ ሁሉ የውጭና የውስጥ ሃይሎችን ሀገር የማዳከም ሴራ በተደራጀ አግባብ መመከትና ማክሸፍ ይኖርበታል።
የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ሰኢድ ሙሐመድ በሰጡት አስተያየት፤አሁን ላይ አንዳንድ የውጭ ሀገራት ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር ጥረት እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።
ሀገሪቱ በተለይ ከህዳሴው ግድብ ጋር ተያይዞ የወደፊት የመልማት እቅዷን ለማጨናገፍ በሚችሉት አቅም ሁሉ እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያን የመልማትና የማደግ ሁኔታ በተለይ አሜሪካን ጨምሮ አንዳንድ የምዕራባዊያን ሀገራት በምስራቅ አፍሪካ ገናና እና ተጽዕኖ ፈጣሪ ትሆናለች በሚል ስጋት ኢትዮጵያን ለማዳከም በማሴር ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል።
የውጭ ሀይሎች የሴራ እንቅስቃሴ ሊገርመን አይገባም፤ ይልቁንም ተልዕኳቸውን የሚያስፈጽሙ እራሳቸውን እንደዜጋ የማይቆጥሩ የውስጥ ሃይሎች አሉ ብለዋል።
ህዝቡ ሀገሪቱ አሁን ላይ ያለችበትን ተጨባጭ ሁኔታ ቆም ብሎ በማየት ከዚህ ቀደም አባቶቹ የእምነትና የፖለቲካ ልዩነት ሳይበግራቸው ከውጭ የሚመጣ ጠላትን በጋራ በመቆም እንዳሳፈሩት ሁሉ ዛሬም ጫናዎችን ለመቋቋም በጋራ መመከት እንዳለበት ሼህ ሰኢድ አሳስበዋል።
አንዳንድ የውጭ ሃይሎች ጥረት የኢትዮጵያን እድገት ለመግታት ህዝቡን በመከፋፈል እርስ በርስ እንዲጋጭ ማድረግ እንደሆነ ጠቁመው፤ግብፅና ሱዳን ከዓባይ ግድብ ጋር ተያይዞ በከፍተኛ ሁኔታ የኢትዮጵያን መዳከምና መፍረስ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።
"ከእነሱ ጀርባ ደግሞ እነአሜሪካ ጣልቃ በመግባት በእኛ ላይ ለማዘዝ የሚሞክሩት ነገር አለ ፤እንደ ሃገር እንዲህ ዓይነት ፈተና ሲገጥመን በአንድ መቆም አለብን" ብለዋል።
በመጪው ሰኞ የሚካሄደው ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ መተማመን የሰፈነበት እንዲሆን ህብረተሰቡ የራሱን ሃላፊነት መወጣት እንዳለበትም መልክት አስተላልፈዋል።
ህዝቡ ይሆነኛል የሚለውን ፓርቲ እንዲመርጥ እድል ተመቻችቶለታል ያሉት ሼህ ሰኢድ፤ መተማመን እንዲፈጠር ህዝቡ እራሱ ታዛቢና ደምጽ ሰጭ በመሆን ሃላፊነቱን እንዲወጣም መክረዋል።
የባህር ዳር ሀገረ ስብከት ዋና ስራ አስኪያጅና የአማራ ክልል የሃይማኖት ተማቋማት ጉባኤ የቦርድ ሰብሳቢ መልአከ ሰላም ኤፍርሬም ሙሉዓለም በበኩላቸው፤አንዳንድ የውጭ ሀገራት ኢትዮጵያን ለማዳከም የሚያደርጉት ፍትሃዊ ያልሆነ አካሄድ ተገቢነት እንደሌለው ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ጠንካራ አገር መሆኗ የሚያስፈራቸው የውጭ ሃይሎች አቅሟን ለማደካም ከቻሉም ለማፈራረስ የጀመሩት ሴራ ዛሬ ላይ የተጀመረ አይደለም ብለዋል ።
በኢትዮጵያ ላይ የሚስተዋላው የአንዳንድ የውጭ ሀገራት ዛቻና ማስፈራራት አዲስ እንዳልሆነ ጠቅሰው፤ የኢትዮጵያ ህዝብ የተለያየ እምነት ይከተል ካልሆነ በስተቀር ሁሉም ሰው በድንበሩና በሀገሩ ዋዛ ፈዛዛ ሆኖ አያውቅም ሲሉ ገልጸዋል።
ህዝቡ መጪው ምርጫ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በራሱ ሃሳብ በመመራት የሚፈልገውን መምረጥ ተገቢ ነው ያሉት መልአከ ሰላም ኤፍሬም ፤ከዛ ውጭ በሆነ አግባብ በመሄድ ሁከት መፍጠር ለሀገርም ሆነ ለራስ እንደማይጠቅም ተናግረዋል።