ቀጥታ፡

ብልጽግና ፓርቲ የህዝቦችን አንድነት በማጠናከር የለውጥ ጉዞውን ዳር ለማደረስ ይሰራል- አቶ ኡሞድ ኡጁሉ

ጋምቤላ ፤ ሰኔ 09/2013 (ኢዜአ) የብልጽግና ፓርቲ የህዝቦችን አንድነትና ወንድማችነት በማጠናከር የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ዳር ለማድረስ እንደሚሰራ የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሜቴ አባል አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ገለጹ።

የብልጽግና ፓርቲ በጋምቤላ ክልል የመጨረሻውን የምረጡኝ ቅስቀሳና የድጋፍ ሰልፍ ዛሬ በጋምቤላ ከተማ አካሄዷል።

በማጠቃለያ መረሃ ግብሩ ላይ የተገኙት  አቶ ኡሞድ ኡጁሉ እንደተናገሩት ፓርቲው የሚመራው መንግስት ባለፉት ዓመታት በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች የተገኙ መልካም ተሞክሮዎችን በማስፋትና ጉድለቶችም በማረም የህዝቦችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሲሰራ ቆይቷል።

ብልጽግና በተለይም የውጪ ጣልቃ ገብነትንና የውስጥ ተባባሪዎቻቸውን በጋራ ክንድ በመመከት የኢትዮጵያን ብሩህ ተስፋ ወደ ላቀ ምዕራፍ ለማሸጋገር በትጋት እየሰራ ያለ ፓርቲ መሆኑም ገልጸዋል።

በቀጣይም ፓርቲው የህዝቦችን አንድነትና ወንድማማችነት በማጠናከር የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ዳር ለማደረስ ይሰራል ብለዋል።

ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ከመቼውም ጊዜ በተለየ ሁኔታ ፍጹም ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ ፍፃሜውን እንዲያገኝ የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች በትጋት እየሰሩ እንደሚገኙም አስታውቀዋል።

መላው የክልሉ ህዝብ በድምጽ መስጪያው ዕለት በነቂስ በመውጣት የድምጽ መስጠትና ችግኝ በመትክል የአረንጓዴ  አሻራ ልማት በጣምራ እንዲያካሄዱም  አቶ ኡሞድ ጥሪ አቅርበዋል።

በብልጽግና ፓርቲ  የጋምቤላ ክልል ቅርጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ላክድር ላክባክ በበኩላቸው ብልጽግና  የማያዳላና ሁሉንም በኩል የሚያይ አካታች የፖለቲካ ፓርቲ መሆኑን ገልጸዋል።

ብልጽግና የህዝቦችን አንድነትና ወንድማማችነት በማጠናከር በመደመር እሳቤ የተጀመረውን የልማትና የብልጽግና ጉዞ ዳር ለማድረስ እየተጋ  እንደሚገኝ  ተናግረዋል።

በስነ-ስርዓቱ ላይ ከተገኙ የፓርቲው አባላት መካከል አቶ ኡዋር አዳር በሰጡት አስተያየት፤ ጥቂት ቀናት  የቀረው  ምርጫ ያላንዳች ችግር  እንዲጠናቀቅ ጠንክረው እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ምርጫው ፍጹም ሰላማዊና ፍትሃዊ  ሆኖ በስኬት ከፍጻሜው አንዲደርስ  ከመንግስታና ሌሎች አካላት ጋር በትብብትር እየሰሩ መሆናቸውን  የተናገሩት ደግሞ ሌላው የመረሃ ግብሩ ታደሚ መምህር ጋሻው ጳውሎስ ናቸው።

በመረሃ ግብሩ ላይ ብዛት ያላቸው  የፓርቲው አባላትና  ደጋፊዎች መገኘታቸውን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከጋምቤላ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም