ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር 4 ሺህ 382 ካሬ ሜትር ቦታ ተረከበ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 09 ቀን 2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 4 ሺህ 382 ካሬ ሜትር ቦታ ተረከበ።

ማህበሩ የሚያስገነባው ህንፃ የመሰረት ድንጋይ በዛሬው እለት ተቀምጧል።

በ2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ወጪ የሚገነባው ህንፃ 2 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የሚያርፍና 32 ወለል ይኖረዋል።

አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ማህበሩ የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ለሚገነባው ህንጻ ከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልፀዋል፡፡

ለህንጻው ግንባታ ማስጀመሪያ አስተዳደሩ 50 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉንም ይፋ አድርገዋል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ጌታሁን መኩሪያ በበኩላቸው መንግስት ለመምህራን ትኩረት በመስጠት የተለያየ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ሚኒስቴሩ ለማህበሩ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን ጠቅሰው፤ በቀጣይም ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ፕሬዚዳንት ዶክተር ዮሃንስ በንቲ፤ የከተማ አስተዳደሩ ለህንፃ መስሪያ ቦታ በመስጠቱ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም