ቀጥታ፡

በታዳሽ ኃይል በመንቀሳቀስ አገልግሎት የሚሰጡ የትራንስፖርት አማራጮችን ለመጠቀም የሚያስችል መሪ እቅድ ተዘጋጀ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 9/2013(ኢዜአ) በታዳሽ ኃይል የሚንቀሳቀሱ የትራንስፖርት አማራጮችን ለመጠቀም የሚያስችል መሪ እቅድ መዘጋጀቱን የትራንስፖርት ሚኒስትር ዳግማዊት ሞገስ ገለጹ፡፡

የታዳሽ ኃይል ትራንስፖርት አገልግሎትን ለማስፋፋት ብሔራዊ አስተባባሪ ኮሚቴ ዛሬ ተቋቁሟል፡፡

በትራንስፖርት ዘርፍ በተዘጋጀው ፍኖተ ካርታ ለታዳሽ ኃይል አገልግሎት የሚሰጡ  የትራንስፖርት አማራጮችን ለመጠቀም መታቀዱን ሚኒስትሯ ገልጸዋል።

ኤሌክትሪክን የሚያካትቱ የታዳሽ ኃይሎችን ለትራንስፖርት አገልግሎት ለማዋል ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሚኒስቴሩ ሥራውን ከሌሎች ተቋማት ጋር ለማቀናጀት ብሔራዊ አስተባባሪ  ኮሚቴ  መቋቋሙንም የተናገሩት ወይዘሮ ዳግማዊት፤ይህም ሥራውን ለማስጀመር ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ገልጸዋል፡፡

የውሃ፣መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በበኩላቸው አገሪቱ ታዳሽ ኃይልን ለመጠቀም ካላት ዕድልና ምቹነት አንጻር በፍጥነት ወደ ተግባር መግባት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በታዳሽ ኃይል የሚንቀሳቀስ የትራንስፖርት አገልግሎት ከአየር ንብረት ለውጥ ባሻገር  በዝቅተኛ ዋጋ ኃይል ለማቅረብ እንደሚያስችል አብራርተዋል፡፡

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል፤ ኢትዮጵያ ታዳሽ ኃይልን በመጠቀም  ለነዳጅ የምታወጣውን ወጪ ለመቀነስ  እንደሚያስችላት ተናግረዋል፡፡

ለአብነትም አንድ የነዳጅ ማደያ ለመገንባት የሚወጣው  ወጭና የሚወስደው  ቦታ  በታዳሽ  ኃይል መሙያ (ቻርጅ) ጣቢያ  ከሚወጣው አንጻር  ከፍተኛ  በመሆኑ  ታዳሽ ኃይልን በፍጥነት ወደ ገበያው ማስገባት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ አውቶሞቲቭ ማህበር ተወካይ አትሌት ኃይሌ ገብረ ሥላሴ  መንግሥት  ታዳሽ ኃይልን ለትራንስፖርት አገልግሎት ለማዋል ድጋፍ  ማድረግ ይገባዋል ብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም