የዘንድሮው ምርጫ የስልጣን ምንጭ ህዝብ መሆኑን ለማረጋገጥ ምቹ አጋጣሚ ነው - ኢዜማ - ኢዜአ አማርኛ
የዘንድሮው ምርጫ የስልጣን ምንጭ ህዝብ መሆኑን ለማረጋገጥ ምቹ አጋጣሚ ነው - ኢዜማ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 09 ቀን 2013 (ኢዜአ) የዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ የስልጣን ምንጭ ህዝብ መሆኑን ለማረጋገጥ ምቹ አጋጣሚ መሆኑን የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) ገለጸ።
ኢዜማ የምርጫ ሂደቱ ከተጀመረ ጀምሮ ባጋጠሙት ተግዳሮቶች ላይ ለመገናኛ ብዙሀን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።
የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ ናትናኤል ፈለቀ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ መንግሥትን ከሕዝብ ፈቃድ ሥር ለማድረግ የሚደረገው ትግል ዛሬም ድረስ እንደቀጠለ ነው።
ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ እውነተኛ የስልጣን ምንጭ ህዝብ መሆኑን ለማረጋገጥ ተወዳዳሪ የማይገኝለት ምቹ አጋጣሚ መሆኑን አብራርተዋል።
የምርጫ ሂደቱ ከተጀመረ ወዲህ በዕጩዎች ምዝገባ፣ በመራጮች ምዝገባ፣ በምርጫ ቅስቀሳ እና በመራጮች መዝገብ ማጣሪያ ጊዜዎች የተለያዩ ተግዳሮቶች ማጋጠማቸወን ገልጸው፤ እነዚህን ጉዳዮች ፓርቲያቸው በየጊዜው ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሲያሳውቅ መቆየቱን አብራርተዋል።
በእጩዎች ምዝገባ ወቅት በየምርጫ ወረዳዎቹ ያሉ የምርጫ ጽሕፈት ቤቶች በተያዘላቸው ጊዜ ሰሌዳ ባለመከፈታቸው፣ ዘግይተው የተከፈቱትም ለበቂ ጊዜ ክፍት ሆነው አለመቆየታቸው መስተዋሉን ያወሱት አቶ ናትናኤል፤ የመራጮች ምዝገባ በተከናወነበት ወቅት የምርጫ ጣቢያዎች በሰዓታቸው አለመከፈት ትልቅ ተግዳሮት ሆኖ መቆየታቸውን አብራርተዋል፡፡
የምርጫ ቅስቀሳ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ባነሮችን ከመቅደድ ጀምሮ አባላቶቻቸውን እስከማሰር የሚደርሱ እክሎች ማጋጠሙን ተናግረዋል ፡፡
ደጋፊዎቻቸውና አባላቶቻቸው ከቅስቀሳ ጀምሮ ላደረጉት አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።
በድህረ ምርጫም የሚገኘውን ውጤት ምንም ይሁን ምን ልፋታቸው ከየትኛውም የምርጫ ውጤት በላይ የሆነ መሆኑን አምነው ሊቀበሉትም እንደሚገባ ተናግረዋል።