በፌዴራል መስሪያ ቤቶች የኤሌክትሮኒክስ ግዥ አሰራር ሊተገበር ነው - ኢዜአ አማርኛ
በፌዴራል መስሪያ ቤቶች የኤሌክትሮኒክስ ግዥ አሰራር ሊተገበር ነው

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 09 ቀን 2013 (ኢዜአ) የፌዴራል የመንግስት ግዥ እና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ በፌዴራል መስሪያ ቤቶች የኤሌክትሮኒክስ ግዥ አሰራር ሊተገብር መሆኑን አስታወቀ።
ኤጀንሲው በ2013 በጀት አመት የእቅድ አፈጻጸም ላይ የታዩ ጉድለቶችን በተመለከተና በ2014 በጀት አመት ሊሰራ ባቀዳቸው ተግባራት ላይ ከ74 የፌዴራል ተቋማት ጋር ውይይት አድርጓል።
የኤሌክትሮኒክ ግዥ አሰራር (ኢጂፕ) ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ሲደረግ በመንግስት ግዥ ስርዓት ውስጥ ክፍተቶችና ጉድለቶች እንዳይፈጠሩ፣ የጨረታ ተደራሽነትን ለማቀላጠፍ፣ ግልጽነትና ውድድር እንዲኖር የሚያስችል እንደሆነ ተጠቁሟል።
በተጨማሪም በስርዓቱ ውስጥ የሰዎች ጣልቃ ገብነት እንዳይኖር የሚያደርግ እንደሆነ ተገልጿል።
የፌዴራል የመንግስት ግዥ እና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ሃጂ ኢብሳ እንደገለጹት፤ የመንግስት የኤሌክትሮኒክ ግዥ ስርዓቱ በዘጠኝ የፌዴራል ተቋማት በሙከራ ደረጃ ተግባራዊ እየተደረገ ነው።
ከ6 ወር በኋላ ደግሞ በ50 የፌዴራል ተቋማት ላይ ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑን ገልጸዋል።
አሰራሩ በሁለት አመት ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ በሁሉም ፌዴራል ተቋማት ተግባራዊ የሚደረግ ሆኑንም ጠቅሰዋል።
በኤጀንሲው የመንግስት ግዥና አስተዳደር ዳይሬክተር ወይዘሮ መቅደስ ብርሃኑ “የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ ስርዓት ተግባራዊ ሲደረግ በተለይ ተአማኒነትን ለማስፈን ትልቅ ጠቀሜታ ይኖረዋል” ብለዋል።
የግዢ ሂደቱ ለችግሮች ያለውን ተጋላጭነት እንደሚቀንስና ግልጽነትን ለማስፈን እንደሚያስችል ተናግረዋል።
ከጊዜ አንጻርም ጠቀሜታ እንዳለው አመልክተዋል።