ለምርጫው ሰላማዊነት ዝግጅት ተጠናቆ ወደ ስራ ተገብቷል- አቶ አገኘሁ ተሻገር - ኢዜአ አማርኛ
ለምርጫው ሰላማዊነት ዝግጅት ተጠናቆ ወደ ስራ ተገብቷል- አቶ አገኘሁ ተሻገር
ባህር ዳር፣ ሰኔ 9/2013 ( ኢዜአ ) ለ6ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊነት አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቆ ወደ ስራ መገባቱን የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ አገኘሁ ተሻገር አስታወቁ።
በባህር ዳር ከተማ የብልፅግና ፓርቲ የ6ኛው ዙር የምርጡኝ ቅስቀሳ ማጠቃለያ ስነ ስርአት ዛሬ ተካሄዷል።
አቶ አገኘሁ ተሻገር በወቅቱ እንዳሉት በምርጫው ምክንያት ምንም ዓይነት የደህንነት ስጋት እንዳይፈጠር ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።
"ምርጫውን ለማደናቀፍ የሚደረጉ ማናቸውም እንቅስቃሴዎች ተቀባይነት የላቸውም" ያሉት ርዕስ መስተዳደሩ በመንግስት በኩል ለምርጫው ሰላማዊነት አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቆ ወደ ስራ መገባቱን አስታውቀዋል።
የአማራን ህዝብ በጎጥ፣ በመንደርና በአካባቢ ለመከፋፈል የሚፈልጉ የስልጣን ጥመኞች በመኖራቸው ህዝቡ ነቅቶ የእነዚህን ሃይሎች አጥፊ ሃሳብ ሊከላከል እንደሚገባ ገልፀዋል።
በተለይም ወጣቶች ተደራጅተው ከፀጥታ መዋቅሩ ጎን በመሆን ሰላም የማስከበሩን ስራ በባለቤትነት ሊሰሩ እንደሚገባ አቶ አገኘሁ አመልክተዋል።
ብልፅግና ፓርቲ ኢትዮጵያ ከገጠማት ውስብስብ ችግር እንድትወጣ ህዝቡን ከጎኑ በማሰለፍ ኢትዮጵያ በሳል አመራር በመስጠት እየሰራ የሚገኝ አሻጋሪ ፓርቲ እንደሆነ ገልፀዋል።
"የክልሉ መዲና በሆነችው ባህር ዳር አስተማማኝ ሰላም በማስፈን፣ ለነዋሪዎች፣ ጎብኝዎች የተመቸች እንዲሁም የቱሪዝም፣ የኢንዱስትሪና የልማት ከተማ እንድትሆን የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍና እገዛም ይሰጣል" ብለዋል።
''ብልፅግና ፓርቲ የተሻለ የአመራር ጥበብ፣ መዋቅር፣ ተደማጭነት፣ ልምድና እውቀት ያለው ፓርቲ ነው'' ያሉት ደግሞ በብልፅግና ፓርቲ የአማራ ክልል ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አብረሃም አለኽኝ ናቸው።
"በብልፅግና ፓርቲ ውስጥ አንዱ ጫኝ፤ አንዱ ተሸካሚ የሚሆንበት እድል የለም" ያሉት አቶ አብረሃም "ቀደም ሲል የተዘራውን መጥፎ የጥላቻ ዘር እየነቀልንና እያቃጠልን በምትኩ መልካም ፍሬ የሚያፈራ ዘር እንዘራለን" ብለዋል።
በተለያዩ የውጭ ሃገራት ያሉ ተከፋዮች ኢትዮጵያ ትፈርሳለች የሚል ምኞት ቢኖራቸውም ''ኢትዮጵያ ለኢትዮጵያ ህዝብ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ለኢትዮጵያ የነፍስና የስጋ ያህል የተሰናሰሉና ሊለያዩ የማይችሉ ናቸው'' ብለዋል።
ይህ ምኞች ዳግም እንዳያንሰራራ የኢትዮጵያ ህዝብ እንደ ከዚህ ቀደሙ እርስ በእርሱ ተጋግዞና ተደጋግፎ ምርጫውን ያለምንም ኮሽታ ማከናወንና የኢትዮጵያን ታላቅነት ዳግም ለዓለም ህዝብ የሚያሳይበት ወሳኝ ወቅት እንደሆነ ተናግረዋል።
አሁን ላይ የአማራ ብሎም የኢትዮጵያ ህዝብ የገጠመውን ፈተና በበሰለ አመራር በመሻገር ላይ መሆኑን አመልክተዋል።
ፓርቲው በእውቀት፣ በአመራር ብቃት፣ በህዝብ አመኔታ ከፍ ያሉ አመራሮችን በምርጫው በእጩነት ማቅረቡን ጠቅሰዋል።
"ለለውጥ ተነስተናል፤ ለውጥም እያመጣን ነው "ያሉት አቶ አብረሃም ፓርቲው ከምርጫ በኋላም ለወጣቱ የስራ እድል ለመፍጠር በትኩረት እንደሚሰራ አስታውቀዋል።
"የባህር ዳር ከተማ በሁለንተናዊ ልማቷ ለዜጎች ኩራትና ምሳሌ ነች" ያሉት ደግሞ የከተማው ተቀዳሚ ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሳህሉ ናቸው።
"በከተማው የነዋሪዎችን የመኖሪያ ቤት ጥያቄ ለመመለስ፣ የመሰረተ ልማት ዝርጋታን በማስፋፋት፣ የስራ እድል በመፍጠር፣ ማህበራዊ ችግሮችን በመፍታትና ሌሎች የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ አመራሩ ቀን ከሌት እየሰራ ይገኛል" ብለዋል።
የልማት ስራዎቹ የከተማዋን የእድገትና ተስፋ ታሳቢ ባደረገ አግባብ ደረጃውን በሚመጥን መንገድ እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው፤ የከተማው ነዋሪ ልማቱ በተሟላ መልኩ እንዲከናወን ተገቢውን እገዛ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
ምርጫው በሰላማዊ መንገድ እንዲከናወን ተገቢው ዝግጅት መደረጉን ገልፀው "ለሰላምና ደህንነቱ የሁሉም ድጋፍ አስፈላጊ ነው" ብለዋል።
በቅስቀሳ ማጠቃለያ ስነ ስርአቱ ላይ የክልሉና የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች እንዲሁም የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች ተገኝተዋል።