የብልጽግና ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳ ማጠቃለያ መረሃ ግብር በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች ተካሄደ - ኢዜአ አማርኛ
የብልጽግና ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳ ማጠቃለያ መረሃ ግብር በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች ተካሄደ
ወልድያ፣ ሰቆጣ፣ መተማና ደብረ ብርሃን፤ ሰኔ 9/2013(ኢዜአ) የብልጽግና ፓርቲ ለስድስተኛ ጠቅላላ ምርጫ ውድድር የምርጫ ቅስቀሳ ማጠቃለያ መረሃ ግብር በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች አካሄደ።
መረሃ ግብሩ የተካሄደው በወልድያ ፣ ሰቆጣ ፣ገንዳ ውሃና ደብረ ብርሃን ከተሞች የፓርቲው አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች በተገኙበት ነው።
በወልድያ ከተማ በተካሄደው መረሃ ግብር የተገኙት የብልጽግና ፓርቲ የሰሜን ወሎ ዞን ከፍተኛ አመራር አቶ ወልደ ትንሣኤ መኮንን ባሰሙት ንግግር፤ ብልጽግና ባለፉት ሶስት ዓመታት ሀገራዊ አንድነትን በመጠበቅ ኢትዮጵያን ከመፈራረስ አደጋ የታደገ ፓርቲ መሆኑን ተናግረዋል።
አገርን ለማፈራረስ በግንባር ቀደምትነት ሲሰራ የነበረውን አሸባሪው ህወሃትን በተባበረ ክንድ በመደምሰስ ሀገርን ከነሙሉ ክብሯ እንድትቀጥል ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ገልጸዋል።
በፓርቲው የወልድያ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራር አቶ መሀመድ ያሲን በበኩላቸው፤ አንዳንድ የውጭ ሃይሎችና አክቲቪስቶች ምርጫው በሰላም እንዳይጠናቀቅ አበክረው ለመስራት ቢሞክሩም አልተሳካላቸውም ብለዋል።
ሕዝቡ በቅድመ ምርጫ ወቅት ችግሮች እንዳይከሰቱ የራሱን ሰላም ለማስጠበቅ ከመንግስት ጎን በመሰለፍ ያበረከተውን አስተዋጽኦ በዕለቱና በድህረ ምርጫ ወቅትም እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
በተመሳሳይም በሰቆጣ ከተማ በተካሄደው የማጠቃለያ መረሃ ግብር ላይ የተገኙት በፓርቲው የከተማዋ አስተዳደር ከፍተኛ አመራር አቶ አሸብር ግርማ ባደረጉት ንግግር፤ ብልፅግና በበርካታ ችግሮች ተፈትኖ የወጣ ፓርቲ ነው ብለዋል።
በወንድማማችነት ላይ የተመሰረተ ህብረ ብሄራዊ ስርዓት በመዘርጋት የዜጎችን ዘላቂ ሰላምና ደህንነት ተጠብቆ የሃገሪቱን እድገት ለማፋጠን እየታተረ ያለ ፓርቲ መሆኑን አብራርተዋል።
በገንዳ ውሃ በተካሄደ መረሃ ግብር በብልጽግና ፓርቲ የምዕራብ ጎንደር ዞን ከፍተኛ አመራር አቶ እንዳለው ማሩ እንደተናገሩት፤ በሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች የህዝቡን ደህንነትና ሰላም ለመጠበቅ ፓርቲው የድርሻውን ይወጣል።
"አደረጃጀቶችን በማጠናከር ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ከመላው ህዝቡ ጋር ተቀናጅተን እንሰራለን" ብለዋል፡፡
በተመሳሳይ በደብረ ብርሃን ከተማ በተካሄደው መረሃ ግብር ላይ ከተሳተፉት መካከል ወይዘሮ ብርሀኔ ወልደሰማያት በሰጡት አስተያየት፤ ምርጫው በሰላማዊ መንገድ እንዲጠናቀቅ ከአካባቢያቸው ህብረተሰብ ጋር እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
የከተማዋ ነዋሪ ወጣት መስታወት አሰፋ በበኩሏ፤ ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የበኩሌን ጥረት አደርጋለሁ ብላለች፡፡