የመገናኛ ብዙሃን የምረጡኝ ቅስቀሳ መርሃ ግብር ውጤታማ ነበር-ፖለቲካ ፓርቲዎችና መገናኛ ብዙሃን - ኢዜአ አማርኛ
የመገናኛ ብዙሃን የምረጡኝ ቅስቀሳ መርሃ ግብር ውጤታማ ነበር-ፖለቲካ ፓርቲዎችና መገናኛ ብዙሃን
ሃዋሳ፣ ሰኔ 9/2013 (ኢዜአ) በመገናኛ ብዙሃን ሲተላለፍ የነበረው የፖለቲካ ፓርቲዎች የምረጡኝ ቅስቀሳ መርሃ ግብር ውጤታማ እንደነበር የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮችና መገናኛ ብዙሃን ገለጹ፡፡
ኢዜአ ካነጋገራቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የዎብን /ዎላይታ ብሄራዊ ንቅናቄ/ ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ማቲዎስ ባልቻ እንደገለጹት በመገናኛ ብዙሃን የተደለደለው ነጻ የአየር ሰዓት ፍትሃዊና መልእክቶችን በተገቢው መንገድ ማስተላለፍ የተቻለበት ነበር፡፡
“በአንድም ይሁን በሌላ ህዝቡ መረጃ የሚያገኘው ከመገናኛ ብዙሃን በመሆኑ ዓላማና ፖሊሲያችንን ከማስተዋወቅ ጀምሮ የምርጫ መልእክቶችን በአግባቡ ያስተላለፍንበት ነበር” ብለዋል፡፡
በደቡብ መገናኛ ብዙሃን በቴሌቪዥን፣ሬዲዮና ንጋት ጋዜጣ እንዲሁም በፋና ኤፍ ኤም ወላይታ ቅርንጫፍ የምርጫ ቅስቀሳቸውን ያደረጉባቸው የመገናኛ ብዙሃን አውታሮች እንደሆኑ ጠቅሰዋል፡፡
በመገናኛ ብዙሃኑ የተላለፉ መልእክቶችን ተከትሎ በርካታ ግብረ መልሶች መገኘታቸውን በበጎ ጎን ያነሱት አቶ ማቲዎስ በክርክር መድረኮች አለመሳተፋቸውን እንደ ክፍተት አንስተዋል፡፡
ነጻ የአየር ሰዓቱን በመጠቀም ረገድ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች እኩል አቅም እንዳልነበራቸው ጠቁመዋል።
ከህዝብ ጋር በአካል በመገናኘት ለሚደረጉ ቅስቀሳዎች በመገናኛ ብዙሃን የሚተላለፉ ቅስቀሳዎች አጋዥ እንደነበሩ የገለጹት ደግሞ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ(ኢዜማ) የሀዋሳ ቅርንጫፍ ተወካይ አቶ ባራና ጨፎሬ ናቸው፡፡
እንደ ኢዜማ በፌደራልም ሆነ በክልል መገናኛ ብዙሃን የተካሄዱ የምረጡኝ ቅስቀሳዎች ውጤታማ እንደነበሩ ተናግረዋል፡፡
ፖሊሲና ስትራቴጂዎቻችንን እንዲሁም እጩዎቻችንን አስተዋውቅንበታል ያሉት ተወካዩ በዘንድሮ ምርጫ መገናኛ ብዙሃን ፍትሃዊ የአየር ሰዓት ድልድል ከማድረግ ጀምሮ ጠንካራ ስራ ማከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡
የወላይታ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ዎህዴግ) ሊቀመንበር አቶ ተክሌ ቦረና በበኩላቸው “በድምጽ መስጫው ቀን መቀያየር ምክንያት በቅስቀሳ ሂደቱ ጥቂት ውስንነቶች ቢኖሩም የተሰጠንን ነጻ የአየር ሰዓት ተጠቅመን የምረጡኝ ቅስቀሳ አድርገናል” ብለዋል፡፡
ፓርቲው ፖሊሲና ዓላማውን በማስተዋወቅ በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ ከማድረግ ባሻገር እጩዎችም እንዲተዋወቁ እድል መፍጠሩን አመልክተዋል፡፡
መገናኛ ብዙሃን ለህዝብ መረጃ የማድረስ ሃላፊነታቸውን በተገቢው መወጣታቸውን ገልጸው “እንደ ፓርቲ ውጤታማነቱን የምንለካው ከድምጽ አሰጣጥ ውጤቱ በኋላ ነው” ሲሉም አመላክተዋል፡፡
በደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የምርጫ ዴስክ ሰብሳቢና የዜናና ወቅታዊ ጉዳዮች ምክትል አዘጋጅ ጸጋአብ ዮሃንስ 21 ሃገራዊና ክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተደለደለላቸው ነጻ የአየር ሰዓት የምርጫ ቅስቀሳ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡
በቴሌቪዥን፣ በሬዲዮና በንጋት ጋዜጣ አማካኝነት የፖለቲካ ፓርቲዎች መልእክቶች ሲተላለፉ እንደነበር ጠቁመው የቅስቀሳ ሂደቱም ውጤታማና 95 በመቶ የተሳካ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ጥቂት የፖለቲካ ፓርቲዎች ከተሰጣቸው የአየር ጊዜ አሳንሶ አንዳንዴም አብዝቶ የመጠቀም ፍላጎት ማሳየታቸውን እንደ ክፍተት አንስተዋል፡፡
በመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ከተፈቀደው ነጻ የአየር ሰዓት በተጨማሪ ድርጅቱ ባዘጋጀው የክርክር መድረክ በተመረጡ ርዕሰ ጉዳዮች ፓርቲዎች የተሳተፉበት የክርክር መድረክ መከናወኑንና የቅስቀሳ ሂደቱም ውጤታማ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች የምረጡኝ ቅስቀሳ ዛሬ ሰኔ 9 ቀን 2013 እንደሚጠናቀቅ ይታወቃል።