በኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ያለው አለም አቀፍ ጫና የአገሪቷን ሉአላዊነት የሚጋፋ ነው - የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ያለው አለም አቀፍ ጫና የአገሪቷን ሉአላዊነት የሚጋፋ ነው - የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት
አዲስ አበባ ሰኔ 09 ቀን 2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ያለው አለም አቀፍ ጫና አግባብነት የሌለውና የአገሪቷን ሉአላዊነት የሚጋፋ መሆኑን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ገለጸ።
ለዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ ካርድ የወሰዱ መራጮች በሙሉ በእለቱ በመገኘት ድምፅ እንዲሰጡም ጥሪ አቅርቧል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በዛሬው እለት ውይይት በማድረግ መግለጫ ሰጥቷል።
በመግለጫውም በኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ያለው አለም አቀፍ ጫና አግባብነት የሌለውና የአገሪቷን ሉአላዊነት የሚጋፋ መሆኑን ጠቅሷል።
ኢትዮጵያ የገጠሟትን ችግሮች ለመሻገር ውስጣዊ ሰላሟን መጠበቅ፣ የጋራ መግባባትና አንድነት መፍጠር፣ የውጭ ግንኙነትን ማጠናከር ትኩረት የሚሰጣቸው ጉዳዮች መሆናቸውን በመግለጫው አመልክቷል።
የፊታችን ሰኞ በሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ የኢትዮጵያን የውስጥና የውጭ ችግሮች በዘላቂነት የሚፈታ በመሆኑ ካርድ የወሰዱ ዜጎች በሙሉ በእለቱ ድምፅ እንዲሰጡም ጠይቋል።
አንዳንድ የውጭ አገራት በኢትዮጵያ ላይ ያላቸው አረዳድ ትክክል እንዳልሆነ የጠቀሰው መግለጫው፤ በተለይም በቅርቡ በአሜሪካ መንግስት የተጣለው የቪዛ እገዳ ትክክል አለመሆኑን ጠቅሷል።
እየደረሰ ያለውን የውጭ ጫና ለመቋቋም የጋራ ምክር ቤቱ አባል የፖለቲካ ፓርቲዎች ልዩነታቸውን ወደ በመተው በጋራ እንዲቆሙም ጠይቋል።
የውጭ ግንኙነቱ ላይ ልዩ ትኩረት በመስጠት በቀጣይ በርካታ ተግባራትን ማከናወን እንደሚገባም ጠቅሷል።
ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ በምታደርገው የሰላም ማስከበርና ተያያዥ ስራዎች ትልቅ ስራ የሰራችና ተሰሚነት ያላት ሃገር መሆኗን አስታውሷል መግለጫው።
በተለይም በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ የሚመጡ ጫናዎች የሃገር ሉዓላዊነት ጉዳይ መሆኑንም የምክር ቤቱ መግለጫ አመልክቷል።
መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ይህንን በመገንዘብ ግድቡ በስኬት እንዲጠናቀቅ የሚጠበቅበትን ሁሉ በማድረግ አገራዊ ግዴታውን እንዲወጣም ጠይቋል።