ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለ148 የግል ዕጩዎች የ50 ሺህ ብር ድጋፍ ለማድረግ ወሰነ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 9/2013 ( ኢዜአ ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለ148 የግል ዕጩዎች የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ለምርጫ ዕለት ወጪያቸው ማካካሻ ገንዘብ እንዲሰጥ ወሰነ።

ከነገ ጀምሮ የትኛውም ፖለቲካ ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳ ማድረግ የማይችል መሆኑንም አስታወቋል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የኮሚዩኒኬሽን አማካሪ ሶሊያና ሽመልስ መግለጫ ሰጥተዋል። 

በመግለጫቸውም ቦርዱ ቀደም ሲል ለፖለቲካ ፓርቲዎች ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸው፤ ነገር ግን ለግል ተወዳዳሪ ዕጩዎች ድጋፍ እንዳልነበር ገልጸዋል።

ለ148 የግል ዕጩዎች የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ የምርጫ ዕለት ወጪያቸው ማካካሻ ገንዘብ እንዲሰጥ ወስኗል።

በዚህም ለፌዴራልና ለክልል ምክር ቤት 148 የግል ዕጩ ተወዳዳሪዎች ለእያንዳንዳቸው 50 ሸህ ብር ድጋፍ ለማድረግ ወስኖ ከተወዳዳሪዎች ጋር ገንዘቡን ለማስገባት መነጋገራቸውን አንስተዋል። 

ቦርዱ ሰኞ ድምፅ የሚሰጥባቸውና የተወዳዳሪዎች ማንነት የያዘ ሰነድ በቦርዱ ድረ ገፅ ላይ ይፋ ተደርጓልም ብለዋል። 

ከነገ ጀምሮ ማንም የምርጫ ቅስቀሳ ማድረግ አይቻልም፤ በሚዲያዎች ከፖለቲካ ፓርቲዎች ቅስቀሳና የፓርቲዎችን ፕሮግራም ማስተዋወቅ አይፈቀድም ብለዋል። 

በመሆኑም በአደባባይም ሆነ በአዳራሽ ሰብሰባዎችን ጨምሮ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የቅስቀሳ መረጃዎችን ማሰራጨት እንደማይችሉ ተናግረዋል።

በቀጣይ ቀናት ስለመራጩ ህዝብ፣ ምርጫ ካርድ፣ ድምፅ አሰጣጥ፣ ድምፅ መስጫ ወረቀቶችን ለመራጮች ግልፅ በማድረግ ረገድ ዘገባዎች ቢሰሩ ይበረታታሉ ነው ያሉት።

ከነገ ጀምሮ ሚዲያዎች ማንኛውንም ከፖለቲካ ፓርቲና ዕጩ ጋር የተገናኙ ዘገባዎችን ማስተናገድ አይችሉም ብለዋል።

በቀጣይ ቀናት ስለ ምርጫ አይቶች፣ ምርጫ ጣቢያዎች፣ ምርጫ ካርድ፣ ድምፅ አሰጣጥ፣ ድምፅ መስጫ ወረቀቶችን ለመራጮች ግልጽ ከማድረግ ረገድ መረጃ ቢያደርሱ ይበረታታሉ ነው ያሉት።

ከምርጫ ጋር በተያያዘ ሀሰተኛ መረጃዎችን ለመከላከል ከፌስቡክ የምስራቅ አፍሪካ ቡድን ጋር በጋራ እየሰራን ነው ብለዋል።

በተለይም በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ መረጃዎችን እውነተኛነት ማረጋገጫና ሃሰተኛ መረጃዎችን ማስወረድ ላይ እንሰራለን ብለዋል።

እስካሁንም ከምርጫው ጋር በተያያዙ ስራዎችን በምርጫ ወቅትና በድህረ ምርጫ ድምጽ ውጤት ላይ የሚነሱ ሀሰተኛ መረጃዎችን በመከላከል በጋራ መስራቱን እንቀጥላለን ብለዋል።

ማንኛውም ዜጋ ሀሰተኛ መረጃዎች ሲሰራጩ ለቦርዱ እንዲያመለክትም ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም