የብሔራዊ ዩኔስኮ ጽህፈት ቤት አዲስ አሰራር ሊዘረጋ ነው

75

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 9 / 2013 /ኢዜአ/ የብሔራዊ ዩኔስኮ ጽህፈት ቤት ስራዎችንና ግንኙነትን በተሻሻለ መልኩ ለማስኬድ አዲስ አሰራር ሊዘረጋ ነው።

ውይይቱን የትምህርት ሚኒስቴር ሰብሳቢ በመሆን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ዩኔስኮ ጽህፈት ቤት የኮሚቴ አባላትና ተወካዮች በተገኙበት መካሄዱ ተገልጿል፡፡

በዚህም በጽህፈት ቤቱ እስካሁን የተሰሩ ስራዎችን እና ያጋጠሙ ችግሮች አስመልክቶ ተወያይቷል፡፡

የትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ጌታሁን መኩሪያ እንደገለጹት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ዩኔስኮ ጽህፈት ቤት የነበሩ ችግሮችን በማረም ቀጣዩን የተሻለ ለማድረግ መስራት ያስፈልጋል፡፡

እንደ ዶክተር ጌታሁን ገለጻ ጽህፈት ቤቱን መልሶ በማደራጀት በቂ እውቀት ባላቸው ባለሙያዎች ይሰራል።

ብሔራዊ ዩኔስኮ ጽህፈት ቤቱ በበኩሉ በሁሉም አባል መስሪያ ቤቶች፣ የተሰሩ ስራዎችን በቀላሉ ለማግኘት፣ እንዲሁም በፓሪስ ከሚገኘው የዩኔስኮ ዋና ጽህፈት ቤት ጋር ለመገናኘት የሚያስችል አዲስ ፕላትፎርም በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚዘረጋ አስረድተዋል፡፡

በፓሪስ የኢፌዴሪ ሚሲዮን ባለሙሉ ስልጣን በሚኒስትር ደረጃ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሳይንስ፣ የትምህርት እና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) ምክትል ቋሚ መልእክተኛ ዶክተር ጥላዬ ጌቴ በበኩላቸው፥ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ዩኔስኮ ጽህፈት ቤት ሰብሳቢነት በአዋጅ የተሰጠው ትምህርት ሚኒስቴር አደረጃጀቱን ማጠናከር ይገባዋል ብለዋል፡፡

በብሔራዊ ዩኔስኮ ጽህፈት ቤት የተሰሩት ስራዎች የተበታተነ መሆኑን ጠቅሰው ይህንን ከመሰረቱ መፍታት እንደሚገባ መግለጻቸውን ከትምህርት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም