ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን እንደሚወጡ የአምቦና አካባቢው ነዋሪዎች ተናገሩ - ኢዜአ አማርኛ
ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን እንደሚወጡ የአምቦና አካባቢው ነዋሪዎች ተናገሩ
ሰኔ 8/2013 (ኢዜአ) በመጪው ሰኞ የሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ በሰላም እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን እንደሚወጡ የአምቦ እና አካባቢው ነዋሪዎች ተናገሩ።
የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳ በአምቦ በከተማ አካሂዷል።
በምርጫ ቅስቀሳው ላይ የምዕራብ ሸዋና የአምቦ ከተማ ነዋሪዎች፣ የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ ኃላፊ አቶ ፍቃዱ ተሰማ፣ የኢትዮጵያ አመራር አካዳሚ ፕሬዚዳንት አቶ አወሉ አብዲ፣ የምዕራብ ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዲሪርሳ ዋቁማ ተገኝተዋል።
በምርጫ ቅስቀሳ ላይ የተሳተፉት ነዋሪዎች መጪው አገራዊ ምርጫ በሳላም እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን እንደሚወጡም በተለይ ለኢዜአ ተናግረዋል።
የአካባቢው ማህበረሰብ ለረዥም ዓመታት በርካታ በደሎች እንደተፈጸመበት ያስታወሱት ነዋሪዎቹ፣ አሁን የሚደረገው ምርጫ የተለየ መልክ እንዳለው ገልጸዋል።
ነዋሪዎቹ ምርጫው ሰላማዊ፣ ፍትሃዊ እና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውንም ነው የገለጹት።
የምርጫ ካርዳቸውን ለአገር እድገት ይጠቀማል የሚሉትን ፓርቲ በመምረጥ መብታቸውን ለመጠቀም መዘጋጃታቸውንም ተናግረዋል።
የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍቃዱ ተሰማ ከቀናት በኋላ የሚካሄደው አገራዊ ምርጫ ፍትሃዊ፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
ዜጎች ድምጻቸውን ለመረጡት ፓርቲ በመስጠት የተጀመረውን ሀገራዊ ለውጥና ልማት ሊያስቀጥሉ እንደሚገባም ጠይቀዋል።
በአገሪቱ ጠንካራ ስርዓት ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረትና ህዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶችን ለማስቀጠል ህብረተሰቡ የበኩሉን እገዛ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል አቶ ፍቃዱ።
"ኢትዮጵያን እናልብሳት" በሚል መሪ ሀሳብ በሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ዜጎች ሚናቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ እዲጠናቀቅ ኢትዮጵያዊያን እያደረጉት ያለውን ድጋፍ አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም ነው የገለጹት።
በፓርቲው የምርጫ ቅስቀሳ ላይ ቁጥራቸው በርካታ የሆነ የምዕራብ ሸዋ ዞንና የአምቦ ከተማ ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።