የኢትዮጵያ የማስታወቂያ ባለሙያዎች ምክር ቤት ተመሰረተ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የማስታወቂያ ባለሙያዎች ምክር ቤት ተመሰረተ
ሰኔ 8/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ የማስታወቂያ ባለሙያዎች ምክር ቤት ተመሰረተ።
ምክር ቤቱ በጉባኤው ማጠቃለያ ላይ ሰባት የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ፣ ሶስት የጠቅላላ ጉባኤ አባላትና አንድ ፕሬዝዳንት መርጧል፡ ፡
መድረኩ በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን አማካኝነት የተዘጋጀ ሲሆን በዘርፉ ለበርካታ አመታት የሰሩ ባለሙያዎች ተሳትፈውበታል፡፡
ምክር ቤቱ የህብረተሰቡን ጥቅም የማይጎዱ ማስታወቂያዎች እንዲሰሩ የሚያስችል ምቹ ሁኔታን መፍጠር አላማው አድርጎ መመስረቱ ተገልጿል።
በዚህም ሙያውን የተመለከቱ ህጎች ማርቀቅና ማጽደቅ እንዲሁም ህጎቹ እንዲጠበቁ ለማድረግ የሚያግዙ ስራዎችን እንደሚሰራ ተመላክቷል።
የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሀመድ እድሪስ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ዘርፉ እንደ ሀገር በኢኮኖሚ እድገቱ ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው ።
የማስታወቂያው ዘርፍ ለሀገሪቱ አጠቃላይ ኢኮኖሚ የማይናቅ ድርሻ እንሚያበረከረትም መሀመድ ገልጸዋል።
የጋራ ምክር ቤቱ መቋቋም ዘርፉን ለበርካታ ዘመናት ሲጎትቱት የነበሩትን ተግዳሮቶች በማስቀረት የባለሙያውን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚረዳ ተናግረዋል።
ከዚህ ባለፈ የዘርፉ ተዋንያን በጋራ እንዲንቀሳቀሱ ለማስቻልና ሙያውን በሕግ አግባብ ለመቆጣጠር ያግዛል ተብሏል፡፡
በተጨማሪ በባለስልጣኑ የማስታወቂያው ዘርፍ ትኩረት እንዲያገኝ ለመስራት ያስችለዋልም ሲሉ አክለዋል።
የምክር ቤቱ አደራጅ ኮሚቴ አባል አቶ ዳንኤል ብርሃኑ በበኩላቸው የምክር ቤቱ መቋቋም ኢንዱስትሪው በልምድ ከመመራት ወጥቶ እውቀት ባላቸው ባለሙያዎች እንዲመራ እድል ይፈጥራል ብለዋል፡፡
ህብረተሰቡን እና የማስታወቂያ ባለሙያዎችን በማቀራረብ መልካም ግንኙነት እንዲኖራቸውና መተማመንን እንዲፈጠሩ ያስችላል ሲሉ አክለዋል።
ምክር ቤቱ በጉባኤው ማጠቃለያ ሰባት የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ፣ ሶስት የጠቅላላ ጉባኤ አባላትና አንድ ፕሬዝዳንት መርጧል፡ ፡
የማስታወቂያ ባለሙያና ጋዜጠኛ ሳምሶን ማሞ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ሆኖ ተሰይሟል፡፡
በንግግሩም በዘርፉ የሚታየውን ተግዳሮት ለመፍታትና ሙያው ተገቢውን ክብር እንዲያገኝ በቁርጠኝነት እንደሚሰራም አረጋግጧል።