አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመንገድ ደህንነት ትምህርት በድህረ - ምረቃ መርሃ ግብር ሊሰጥ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመንገድ ደህንነት ትምህርት በድህረ - ምረቃ መርሃ ግብር ሊሰጥ ነው
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 8 ቀን 2013 ( ኢዜአ) የትራንስፖርት ሚኒስቴር በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመንገድ ደህንነት የድህረ - ምረቃ መርሃ ግብር ለመጀመር የመግባቢያ ስምምነት ዛሬ ተፈራረመ።
ስምምነቱን የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና ተፈራርመዋል።
ሚኒስትሯ በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይ እንደተናገሩት ስምምነቱ በመንገድ ደህንነት ዘርፍ በአገር ውስጥ የሰለጠነ የሰው ኃይል ማፍራት ያስችላል።
በዚህም በዘርፉ የሚታየውን ችግር ለማቃለልና በትራፊክ አደጋ የሚደርሰውን ጉዳት መቀነስ እንደሚቻል አስረድተዋል።
ፕሮፌሰር ጣሰው በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው የትምህርት መርሃ ግብሩን ለመጀመር በቅድሚያ የሥርዓተ ትምህርት /ካሪኩለም/ ቀረጻ እንደሚከናወን ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው ሚኒስቴሩ በዘርፉ ለሚያከናውናቸው ሥራዎች ድጋፍ እንደሚያደርግም ተናግረዋል።
የትራንስፖርት ሚኒስቴር ከ2014 ጀምሮ የመንገድ ደህንነትን በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ በማካተት ለመስጠት ትናንት ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር ስምምነት ተፈራርሟል።