ቀጥታ፡

በአዲስ አበባ ህብረተሰቡ ለህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ቀጥሏል

አዲስ አበባ ሰኔ 8/2013 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ ህብረተሰቡ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠሉን በመዲናዋ የግድቡ ግንባታ ህዝባዊ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በዘንደሮው ክርምት ለማካሄድ መታቀዱ ይታወቃል።

ይህንኑ ተከትሎ ለግድቡ ግንባታ ህዝቡ የሚያደርገውን ድጋፍና አስተዋጽኦ ይበልጥ አጠናክሮ መቀጠሉን በአዲስ አበባ ከተማ የህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ምስክር ነጋሽ ገልጸዋል።

በበጀት ዓመቱ የአዲስ አባባ ከተማ ነዋሪዎች ለግድቡ ግንባታ ሂደት የቦንድ ግዢና የጥሬ ገንዘብ ማሰባሰብን ጨምሮ 739 ሚሊየን ብር ለማሰባሰብ እቅድ መያዙን አስታወሰዋል።

ይሁን እንጂ በበጀት ዓመቱ ተይዞ ከነበረው እቅድ በላይ መሰብሰቡን አቶ ምስክር ገልጸዋል።

እቅዱን ለማሳካት ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤቱ የተለያዩ የህዝብ ንቅናቄ ተሳትፎ በመንደፍ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል ብለዋል።

በዚህም በበጀት ዓመቱ ተይዞ ከነበረው እቅድ በላይ ገንዘብ መሰብሰቡን አቶ ምስክር ገልጸዋል።

ባለፉት ሰባት ወራት ከህብረተሰቡ በተገኘ የቦንድ ግዢና የገንዘብ መዋጮ ከ2 ቢሊየን ብር በላይ መሰብሰቡን ተናግረዋል።

ይህም ህብረተሰቡ ለግድቡ የግንባታ ሂደት የሚያደርገውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ መቀጠሉን ያረጋገጠ መሆኑን ገልጸዋል።

እስካሁን እየተደረገ ያለውን ተሳትፎ አመስግነው፤ በቀጣይም ህዝቡ፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሁል ጊዜ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ አሁናዊ አፈፃፀም 80 በመቶ መድረሱ ይታወቃል።

የግንባታ ሂደቱ ከተጀመረ አስር ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን በ2015 ዓ.ም ሙሉ ለሙሉ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም