በኢትየጵያ ላይ የሚቃጣ የውጭ ጣልቃ ገብነት እንደሚቃወሙ በጋምቤላ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትየጵያ ላይ የሚቃጣ የውጭ ጣልቃ ገብነት እንደሚቃወሙ በጋምቤላ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ
ጋምቤለ፤ ሰኔ 08/2013(ኢዜአ) ኢትዮጵያ ከድህነት ለመውጣትና ሰላሟን ለማስጠበቅ እያከናወነች ያለውን ጥረት ለማደናቀፈ እየተቃጣ ያለውን የውጭ ጣልቃ ገብነት አጥብቀው እንደሚቃወሙ በጋምቤላ ክልል አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ።
ፓርቲዎቹ ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌትና ለስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬት የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናገረዋል።
የጋምቤላ ህዝቦች ነፃነት ንቅናቄ /ጋህነን/ ፀሐፊ አቶ ተዘራ ኃይለማሪያም፤ በሀገር ላይ የሚቃጣ ማንኛውም የውጭ ጣልቃ ገብነትና ተጽዕኖ ለመመከት ሁላችንም በአንድነት ልንሰራ ይገባል ብለዋል።
አሜሪካ ጨምሮ አንዳንድ የምዕራባዊያን ሀገራት ኢትዮጵያ በምታከናውናቸውን የሰላምና ልማት ስራዎች ላይ የሚደረጉትን ጣለቃ ገብነት ፓርቲያቸው በጽኑ እንደሚያወግዝ አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በማንም የውጭ ጣልቃ ገብነት እንደማይደፈር የተናገሩት አቶ ተዘራ፤ ይህን የሚያስቡ ካሉም ከመንግስት ጎን በመሆን አሳፍረን መመለስ ይጠበቅብናል ሲሉ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ዜጎቿን ከድህነት ለማውጣት እየሰራች ባለው የታላቁ የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ማንም አድርጉ አታደረጉ ሊል አይገባም ያሉት አቶ ተዘራ በቅርቡ የሚካሄደው ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ኢትዮጵውያን የሚጠባበቁት ድል መሆኑን አወስተዋል።
ሁሉም ኢትዮጵያዊ የታላቁን የህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት፣ ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊና ፍትሃዊ በሆነ መልኩ በስኬት በማጠናቀቅ የውስጥና ውጭ ጠላቶችን ለማሳፋር በአንድነት መስራት ይገባናል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ /ኢዜማ/ የጋምቤላ ቅርንጫፍ ምክትል መሪ ኮማንደር ጋደቤል ቦል በበኩላቸው፤ አሸባሪው ህወሓት በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ መንግስት በወሰደው ህግ የማከበር እርምጃ አሜሪካ ጣልቃ ለመግባት የምታደረገው ሙከራ ሉአላዊነትን መደፈር ነው ብለዋል።
በህዝብ ገንዘብና ጉልበት እየተገነባ ባለው ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግብጽ ጫና ለማሳደር የምታደረገው ጥረት ኢዜማ አጥብቆ ይቃወማል ያሉት ኮማንደር ጋደቤል፤ ለግድቡ ግንባታ እውን መሆን ፓርቲያቸው ከመንግስት ጎን መሆኑን አስታውቀዋል።
አሜሪካ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይና በታላቁ የህዳሴ ግድብ ጣልቃ ለመግባት እያደረገች ያለው ሙከራ ተገቢ አይደለም ያሉት ደግሞ የጋምቤላ ህዝቦች ፍትህ፣ ሰላም፣ ልማት፣ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ/ጋህፍሰልዴን/ ስራአስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ወይዘሮ ኛኒያል ጋላንግ ናቸው።