የመተከል ዞንን የትርምስ ቀጠና በማድረግ የህዳሴ ግድብ ግንባታን ለማስተጓጎል የሚጥሩ ሃይሎች ፈፅሞ አይሳካላቸውም- ብርጋዴል ጄኔራል አለማየሁ ወልዴ - ኢዜአ አማርኛ
የመተከል ዞንን የትርምስ ቀጠና በማድረግ የህዳሴ ግድብ ግንባታን ለማስተጓጎል የሚጥሩ ሃይሎች ፈፅሞ አይሳካላቸውም- ብርጋዴል ጄኔራል አለማየሁ ወልዴ
ሰኔ 07/2013(ኢዜአ) የመተከል ዞንን የትርምስ ቀጠና በማድረግ የህዳሴ ግድብ ግንባታን ለማስተጓጎል የሚጥሩ የውስጥም ይሁን የውጭ ሃይሎች ፈፅሞ የማይሳካላቸው መሆኑን የሀገር መከላከያ ሰራዊት ምዕራብ እዝ ምክትል አዛዥና የኮማንድ ፖስቱ አባል ብርጋዴል ጄኔራል አለማየሁ ወልዴ ገለጹ።
በኢትዮጵያ ውስጥ ህግና ስርዓትን አክብሮ መንቀሳቀስ የሁሉም ዜጋ ግደታና ሃላፊ
ነት መሆኑንም ተናግረዋል።
በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን ባለፉት ዓመታት ይከሰቱ በነበሩ ተደጋጋሚ ግጭቶች በዜጎች ህይወት፣ ማህበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ጫና ማሳደሩ ይታወሳል።
ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት እልባት ለመስጠትም መንግስት የተቀናጀ ግብረ ኃይል በማቋቋም የተለያዩ ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል።
ኮማንድ ፖስቱ እየወሰዳቸው ባሉ እርምጃዎችም ዞኑ ከነበረበት ግጭትና አለመረጋጋት ወጥቶ ወደ አንጻራዊ ሰላምና መረጋጋት እየመጣ ነው።
ታጥቀው ጫካ ገብተው ለነበሩ አካላት ሰላማዊ ጥሪ በማቅረብ የተሃድሶ ስልጠና እንዲወስዱ እየተደረገ ሲሆን አሁን ላይ ለ1 ሺህ 600 ታጣቂዎች የ2ኛ ዙር የተሃድሶ ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል።
በህገ-መንግስት እና ህብረብሄራዊ ወንድማማችነት ዙሪያ ዛሬ እየተደረገ ባለው ገለፃ ላይ የምዕራብ እዝ ምክትል አዛዥና የኮማንድፖስቱ አባል ብርጋዴል ጄኔራል አለማየሁ ወልዴ መልእክት አስተላልፈዋል።
በንግግራቸውም በኢትዮጵያ ህግና ስርዓትን አክብሮ መንቀሳቀስ የሁሉም ዜጋ ግደታና ሃላፊነት መሆኑን አብራርተዋል።
ህግና ህገ- መንግስታዊ ስርዓቱ ካልተከበረ የተወሳሰበ ሀገራዊ ችግር ያስከትላል ብለዋል ብርጋዴል ጄኔራል አለማየሁ።
የውስጥና የውጭ ኃይሎች በተለይ የመተከል ዞንን የትርምስ ቀጠና በማድረግ በህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ ጫና ለማሳደር እየጣሩ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
በኢትዮጵያዊያን አንጡራ ሃብት የሚገነባውን የህዳሴ ግድብ ለማስቆም የሚፈልጉ ቅጥረኞች የተለያዩ ጥረቶችን አድርገዋል ግን ፈፅሞ አይሳካላቸውም ብለዋል።
የህዳሴ ግድብ ግንባታ ለአፍታም ቢሆን ግንባታው ሊቆም አይችልም ሲሉም አረጋግጠዋል።
የጁንታው ሃይል ባለፉት ዓመታት የግድቡን ግንባታ ለማደናቀፍ የተለያዩ አካላትን በማደራጀት ግጭትና ሁከት መፍጠሩን አስታውሰዋል።
በዞኑ የተጀመረው የሰላም ግንባታ ስራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሁሉም በአብሮነት ወደ ልማት ስራዎች መግባት ይጠበቃል ብለዋል ብርጋዴር ጄኔራል አለማየሁ።
ከትጥቅ እንቅስቃሴ ወጥተው ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ የተመለሱት ዜጎችም ለአብሮነትና ልማት ዝግጁ እንዲሆኑ መክረዋል።
የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ሰላምና ደህንነት ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዮት አልቦሮ፤ የህገ መንግስቱን እሴት፣ አላማ፣ ተግባርና አጠቃላይ ድንጋጌ በሚመለከት አብራርተዋል።
የህገ መንግስት መከበርና የህግ የበላይነት መረጋገጥ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን በመገንባት ፈጣን አገራዊ እድገትን ለማምጣት አይነተኛ መሳሪያ መሆኑንም አመላክተዋል።
ለዚህም ሁሉም ዜጋ ለዘላቂ ሰላምና መረጋጋት የሚችለውን ዋጋ ሁሉ በመክፈል ኢትዮጵያ ለያዘችው አገራዊ ለውጥ የበኩሉን አስለዋጽኦ ማበርከት አለበት ብለዋል።
የመተከል ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጋሹ ዱጋዝ፤ ሰልጣኞቹ ከተሃድሶ ስልጠናው በኋላ ስለሚኖሩ የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ገለጻ አድርገዋል።