ቀጥታ፡

ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ለ45ሺህ የአገር ውስጥ የምርጫ ታዛቢዎች ፍቃድ ሰጠ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 14/2013(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የዘንድሮውን ጠቅላላ ምርጫ ለሚታዘቡ 45 ሺህ የአገር ውስጥ ታዛቢዎች ፍቃድ መስጠቱን አስታወቀ።

ቦርዱ በቀጣይ ሳምንት ሰኞ ለሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ በሳምንቱ የተከናወኑ ዋና ዋና ጉዳዮችን ይፋ አድርጓል።

የቦርዱ የኮሙንኬሽን ሃላፊ ሶሊያና ሽመልስ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፣ የአገር ውስጥ የምርጫ ታዛቢዎችን የሚያሰማሩት የሲቪክ ማህበራት መሆናቸውን ገልጸዋል።

የምርጫ ታዛቢዎቹ የሲቪክ ማህበራት፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ በምርጫና በዴሞክራሲ ላይ የሚሰሩ እንዲሁም ከሴቶች ማህበራትና ከአካል ጉዳተኛ ማህበራት በጥምረት የተወከሉ እንደሆኑ ተገልጿል።

በዚህም ቦርዱ ለ45 ሺህ የአገር ውስጥ የምርጫ ታዛቢዎች ባጅ መስጠቱን የኮሙንኬሽን ሃላፊዋ አንስተዋል።

ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም በሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ በ44 ሺህ 372 የምርጫ ጣቢያዎች ድምፅ እንደሚሰጥ ገልጸዋው፤የምርጫ አስፈጻሚዎች ስልጠና እየተካሄደ መሆኑንም አንስተዋል።

የድምጽ መስጫ ቀን የስራ እለት በመሆኑ በምርጫ ህጉ መሰረት ስራ ዝግ ሆኖ መራጮች ድምፅ እንዲሰጡ የመተባበር ግዴታ መኖሩንም አብራርተዋል።

የድምጽ መስጫ ወረቀት ከዛሬ ጀምሮ ለምርጫ ጣቢያዎች እንደሚሰራጭም ተጠቁሟል።

በተለያዩ ችገሮች ሰኔ 14 ድምፅ የማይሰጥባቸው አካባቢዎች ጳግሜን 1 ቀን 2013 ዓ.ም ምረጫ እንደሚካሄድ ቦርዱ መግለጹ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም