በአዲስ አበባ ሶስት ታሪካዊ ህንፃዎች በ2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር እድሳት ሊደረግላቸው ነው

አዲስ አበባ ሀምሌ 27/2010 በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውስጥ የሚገኙ ሶስት ታሪካዊ ህንፃዎችን በ2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ወጪ ለማደስ ማቀዱን የአስተዳደሩ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ። ባለፈው በጀት ዓመት ሥራቸው የተጀመረው የዳግማዊ ምኒልክ ሀውልት እና ለአጼ ቴዎድሮስ መታሰቢያ የታነፀው ሴባስቶፖል ሀውልት እድሳት ሥራም ተጠናቋል። የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አማካሪ አቶ ፀጋ ተማም ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በተያዘው የበጀት ዓመት እድሳት የሚደረግላቸው የቀድሞው ማዘጋጃ ቤት፣ የሼህ ሆጀሌ አል ሀሰን ቤተ-መንግስት እና የመጀመሪያው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መስሪያ ቤት የነበረው የወልደጻዲቅ ጎሹ መኖሪያ ቤት ናቸው። እነዚህ ጥንታዊ ህንፃዎች ታሪካዊ የመዲናዋ መገለጫና የቱሪስት መስህብ የሆኑ ቅርሶች ናቸው። ለታሪካዊ ቤቶቹ እድሳት በአሁኑ ወቅትም የዲዛይን ስራው በከፊል እየተጠናቀቀ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ የዲዛይን ሥራውን ባለፈው በጀት ዓመት ለማጠናቀቅ የታቀደ ቢሆንም በታሪካዊ ቤቶቹ ውስጥ ለሚገኙት ነዋሪዎች ምትክ ቤት የማፈላለጉ ተግባር በወቅቱ ሊሳካ ባለመቻሉ ሥራው መጓተቱን አመልክተዋል። ሆኖም በዚሀ ዓመት ችግሩን በመፍታት ዲዛይኑን በቶሎ ለማጠናቀቅና እድሳቱንም በቅርቡ ለመጀመር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ባለፈው የበጀት ዓመት እድሳታቸው የተጀመረው የዳግማዊ ምኒልክና የአጼ ቴዎድሮስ መታሰቢያ ሀውልቶች ሥራ እየተጠናቀቀ ነው። በጠቅላላው 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገለት የሃውልቶቹ እድሳት በጥር 2010 ዓ.ም ተጀምሮ በዘጠኝ ወር ውስጥ ለማጠናቀቅ ታቅዶ የነበር ቢሆንም ሥራው ከተያዘለት ጊዜ በፊት መጠናቀቁን አቶ ጸጋ ተናግረዋል፡፡ የሀውልቶቹ እድሳት የተከናወነው ታሪካዊ ይዘታቸውን በጠበቀ መልኩ በጥናት ላይ በተመሰረተ የባለሙያዎች እገዛ መሆኑንም አቶ ጸጋ ገልጸዋል፡፡ በአዲስ አበባ ከ13 በላይ በሚሆኑ አደባባዮች የተለያየ የታሪክ ይዘት ያላቸው መታሰቢያ ሀውልቶች ይገኛሉ፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም