ባንኩ በሊዝ ፋይናንስ የብድር አገልግሎት 144 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ለመስጠት መዘጋጀቱን ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ባንኩ በሊዝ ፋይናንስ የብድር አገልግሎት 144 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ለመስጠት መዘጋጀቱን ገለጸ
ጋምቤላ ፤ ሰኔ 07/2013(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በጋምቤላ ክልል ለ18 አነስተኛና መካከለኛ ኢንትራይዝ ፕሮጀክቶች በሊዝ ፋይናንስ የብድር አገልግሎት 144 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ለመስጠት መዘጋጀቱን ገለጸ።
ባንኩ ለአነስተኛና ለመከካለኛ ኢንተርፕራይዞች በጋምቤላ ከተማ ላለፉት አምስት ቀናት ሲሰጥ የቆየው የአቅም ግንባታ ስልጠና ተጠናቋል።
በስልጠናው ማጠቃለያ ላይ በባንክ የጋምቤላ ዲስትሪክት ስራ አስኪያጅ አቶ ኤፍራም ታደሰ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ባንኩ ያዘጋጀው የሊዝ ፋይናንስ ብድር አገልግሎት በእርሻ፣ ኢንዱስትሪ፣ ማዕድን ልማትና ሌሎች ዘርፎች ለተሰማሩ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ለመስጠት ነው።
ይህም በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ዙር ስልጠና ወስደው የባንኩን መስፈርት አሟልቶ ለተገኙ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች እንደሚሆን ገልጸዋል።
ባንኩ ቀደም ሲል በክልሉ ለእርሻ የፕሮጀክቶች የተሰጠው የፋይናንስ የብድር አገልግሎት ዓይነት ችግሮች በሊዝ ፋይናንስ አገልግሎቱ እንዳይደገም በጥንቃቄ እየተሰራ መሆኑም አስረድተዋል።
የሊዝ ፋይናንስ የብድር አገልግሎቱ በክልሉ ዘርፉን በማጠናከር ለመደገፍ ከሚያደረገው ጥረት ጎን ለጎን ቀደም ሲል ለእርሻ ፕሮጀክቶች የተሰጠው ብድር ለማስመለስ እየሰራም ነው ብለዋል።
በክልሉ ከ2006ዓ.ም. ጀምሮ መሬት በማሲያዝ ብድር ወስደው ከተሰወሩ 65 ባለሃበቶች መካከል 40 የሚሆኑ ባለሃብቶች ንብረት መያዙና በህግ አግባብ ለመጠየቅም መረጃዎች ተደራጅተው ለባንኩ የህግ አገልግሎት መላኩን አቶ ኤፍራም አስታውቀዋል።
ከሰልጣኞቹ መካከል አቶ ኡጂኒ ኡዴር በሰጡት አስተያየት፤ በባንኩ የተሰጠው ስልጠና ለኢንተርፕራይዞቹ ብቻ ሳይሆን የባንኩ አሰራር ጭምር ውጤታማ ለማድረግ ያግዛል ብለዋል።
ከአሁን በፊት ይህን መሰል ስልጠና ባለመሰጠቱ ለእርሻ ፕሮጀክት ብድር የወሰዱ ባለሃብቶች ስኬታማ ሳይሆኑ መቅረታቸውን ጠቅሰው፤ ከስልጠናው ያገኙትን ግንዛቤ በመጠቀም በተሰማሩት የግብርና ልማት ውጤታማ ለመሆን እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
ልማት ባንክ የሰጠው ስልጠና ብድር በማግኘት አዋጭ ፕሮጀክት ቀርጸው በተሰማሩበት ዘርፍ ውጤታማ ስራ ለማከናውን እንደሚያግዛቸው የገለጹት ደግሞ ሌላው የስልጠናው ተሳታፊ አቶ ሙሃባ ከድር ናቸው።
ባንኩ ባዘጋጀው ስልጠና በክልል የሚገኙ ከ100 በላይ የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾች መሳተፋቸውን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከጋምቤላ ዘግቧል።