ቀጥታ፡

የቴክኒክና ሙያ መስክን በማጠናከር ለአገር ኢኮኖሚ ያለውን አስተዋጽኦ ለማሳደግ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 2013 (ኢዜአ) የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠናን በማጠናከር ለአገር ኢኮኖሚ ያለውን አስተዋጽኦ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኤጀንሲ አስታወቀ።
የምስራቅ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ "ለላቀ ውጤት እውቅና" በሚል መሪ ቃል የላቀ አስተዋጾኦ ላበረከቱ አሰልጣኞች፣ ሰልጣኞችና ባለሙያዎች የእውቅና አሰጣጥ መርሃ ግብር አካሂዷል።

የአዲስ አበባ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ንጋቱ ዳኛቸው በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣ የአገር ኢኮኖሚን ለማሳደግና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማሳለጥ የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ከፍተኛ ድርሻ አለው።

በዘርፉ ብቃት ያለው፣ ተወዳዳሪና በስነ-ምግባር የታነጸ የሰው ኃይል ለማፍራት በትኩረት መስራት እንደሚገባም ተናግረዋል።

የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ዘርፉን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እና ብቁና ሥራ ፈጣሪ ዜጋ ለማፍራት እየተሰራ መሆኑንም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

"ዘርፉን በማጠናከርና በቴክኖሎጂ የታገዘ በማድረግ ለአገር ኢኮኖሚ የሚያደርገውን አስተዋጽኦ ለማሳደግ እየተሰራ ይገኛል" ሲሉም አክለዋል።

የቴክኒክና ሙያ ተቋማትን በሰው ሃይል፣ በቁሳቁስ እና ግንባታ በማካሄድ የማጠናከር ሥራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፣ "ከተማ አስተዳደሩ ይህን አጠናክሮ ይቀጥላል" ብለዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት በአገር አቀፍ ደረጃ በተደረገ ውድድር ቀዳሚ መሆናቸውን አስታውሰው፣ በቀጣይም ይህን ለማጠናከር እንደሚሰራ ገልጸዋል።

የምስራቅ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የላቀ ሥራ ላከናወኑ አሰልጣኞችና ሰልጣኞች የሰጠው እውቅና የበለጠ ለመስራት የሚያነሳሳ ነው።

በጥናትና ምርምር እንዲሁም በፈጣራ ሥራዎች ላይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባም አሳስበዋል።

የምስራቅ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን አቶ ዮሐንስ ሁንዱማ በበኩላቸው ውጤት ተኮር ስልጣናን በማጠናከር የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማሳለጥ እየተሰራ ነው።

"የስልጠና ጥራት አግባብነትን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል" ያሉት ዲኑ፣  በዚህም ኮሌጁ በጨርቃ ጨርቅ፣ በቆዳ፣ በሆቴልና ቱሪዝም፣ በብረታ ብረትና በአይ.ሲ.ቲ ዘርፎች ጥሩ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን ገልጸዋል።

ኮሌጁን ከተለያዩ ኢንዱስትሪዎች ጋር ለማስተሳሰር ከተለያዩ ተቋማት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በመርሃ ግብሩ በተቋሙ የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ አስልጣኞች፣ ሰልጠኞችና ከ25 ዓመት በላይ ላገለገሉ አሰልጣኞች የሜዳሊያና የዋንጫ ሽልማት መበርከቱን ተናግረዋል።

እውቅና የተሰጣቸው የኮሌጁ አስልጣኞችና ሰልጠኞች በበኩላቸው ሽልማቱ በቀጣይ ለበለጠ ሥራ እንዲነሳሱ የሚረዳቸው መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም