ልዩነቶችን በመተው በሃገር ሉአላዊነትና ጥቅም ላይ የሚሰነዘሩ የውጭ ተጽዕኖዎችን በጋራ መከላከል ይገባል… የኢትዮጵያ የፖለቲካ የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት - ኢዜአ አማርኛ
ልዩነቶችን በመተው በሃገር ሉአላዊነትና ጥቅም ላይ የሚሰነዘሩ የውጭ ተጽዕኖዎችን በጋራ መከላከል ይገባል… የኢትዮጵያ የፖለቲካ የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት
አዳማ፤ሰኔ 7/2013(ኢዜአ)የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሌሎች አካላት የፓርቲ ልዩነቶቻቸውን ወደ ጎን በመተው በሃገር ሉአላዊነትና ጥቅም ላይ የሚሰነዘሩ የውጭ ሃይሎችን ተጽዕኖ ለመከላከል በጋራ እንዲሰሩ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አሳሰበ።
ምክር ቤቱ ይህን ያሳወቀው በቢሾፍቱ ከተማ ሰሞኑን በቅድመና ድህረ ምርጫ አካሄድ፣ በፀጥታ፤ በምርጫ ቦርድና በምርጫ አስፈፃሚዎች ገለልተኘነት፣ በህግ ማስከበርና ወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ ከመከረ በኋላ ባወጣው ባለ 13 ነጥብ መግለጫ ነው።
በመግለጫው ላይም የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሌሎችም ልዩነቶቻቸውን ወደ ጎን በመተው በሃገር ሉአላዊነትና ጥቅም ላይ የሚሰነዘሩ የውጭ ተጽዕኖንዎችን በጋራ እንዲከላከሉ ጠይቋል።
መንግስትም ችግሩን ለመፍታትና የውጭ ኃይሎች እየፈጠሩ ያሉትን ዲፕሎማሲያዊ ጫና ለመከላከል ጠንካራ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ስራ እንዲሰራ ምክር ቤቱ በመግለጫው ጠይቋል።
6ኛው ሃገራዊ ምርጫ እስከሚካሔድበት እለት ድረስ በቀሩት ቀናት በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የተሻለ ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር የሚመለከታቸው የሰላምና ፀጥታ አካላት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሚዲያ ተቋማት እንዲሁም መላው ህዝቡ ለሰላምና ጸጥታ መከበር የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠይቋል።
የሃገራችን የጸጥታ፣ የደህንነት እና የፍትህ አካላት ምርጫው በሰላም ተካሒዶ ይጠናቀቅ ዘንድ ከፖለቲካ ወገንተኝነት በራቀ መልኩ ነጻና ገለልተኛ አገልግሎት እንዲሰጡ የጠየቀው መግለጫው፤ በምርጫው ሂደት የእጩዎችና የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ደህንነት ለማረጋገጥ በትኩረት እንዲሰራም አመልክቷል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ሒደት ላጋጠሟቸው ችግሮችና ለቦርዱ ላስገቡት ማመልከቻ ከምርጫው በፊት ምላሽ እንዲሰጥ የጠየቀው መግለጫው፤ በየአካባቢው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎችም በየአካባቢያቸው የጋራ ምክር ቤት በማቋቋምና በማጠናከር ያለባቸውን ሃላፊነት እንዲወጡ አሳስቧል።
ምርጫው በትግራይ ባይካሔድም በክልሉ በተፈጠረው ችግር በህዝብ ላይ የደረሰው ሰብዓዊ ቀውስ በአፋጣኝ እንዲቆም የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደርና የፌዴራል መንግስት ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ የጠየቀው መግለጫው፤ የደረሰውን ሰብዓዊ ጉዳት በገለልተኛ አካላት ተጣርቶ ለፍትህ እንዲቀርብም አመልክቷል።
በጸጥታና በሌሎች ችግሮች ምክንያት ምርጫ በማይካሔድባቸው አካባቢዎች ያሉ ችግሮች በአፋጣኝ ተወግደው ምርጫው በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ከመስከረም 30 በፊት እንዲካሔድ እንዲያደርግም ምክር ቤቱ በመግለጫው አስታውቋል።
ከምርጫው ቅስቀሳ ጋር ተያይዞ በተለያዩ አካባቢዎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ያጋጠሟቸውን ችግሮች በቀሪ ቀናት የምርጫ ቅስቀሳ ስራቸውን በሰላም ማካሔድ እንዲችሉ የመንግስት አካላት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የማንነት ጥያቄ ህዝበ ውሳኔ የህዝቡ የክልል ጥያቄ መልስ የሚሰጥበት ሒደት መሆኑን ያስታወቀው መግለጫው፤ ይሄንን የህዝብ ጥያቄ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ቅስቀሳ ግብዓት ከማድረግ እንዲቆጠቡም አሳስቧል።
የምርጫውን ውጤት ይፋ የማድረግ ስራ በአዋጅ ቁጥር 1162/2011 መሰረት ስልጣን ባለው የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሊካሔድ ይገባል ያለው የጋራ ምክር ቤቱ መግለጫ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ መገናኛ ብዙሃንና ሌሎችም ህዝብን በማሳሳት ለግጭት እንዳያጋልጡ ሊጠነቀቁ እንደሚገባም ምክር ቤቱ በመግለጫው አስታውቋል።
በሃገራዊ ምርጫው ላይ መሳተፍ የዜግነት መብት መሆኑን ያስታወሰው የጋራ ምክር ቤቱ መላው ህዝብ ይሔንን ሰብዓዊና የዴሞክራሲያዊ መብት መገለጫ በሆነው በዘንድሮው ምርጫ በመሳተፍ ሃገረችንን ካጋጠሟት ችግሮች ለማላቀቅ የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርቧል።