ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎችን ለዘላቂ ሰላም መጠቀም ይገባል-- ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነ እየሱስ ሱራፌል - ኢዜአ አማርኛ
ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎችን ለዘላቂ ሰላም መጠቀም ይገባል-- ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነ እየሱስ ሱራፌል
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 7/2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ያሉ ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎችን ለዘላቂ ሰላም መስፈን መጠቀም እንደሚገባ የኢትዮጵያ ዕርቀ ሰላም ኮሚሽን ሰብሳቢ ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነ እየሱስ ሱራፌል ጥሪ አቀረቡ።
የኢትዮጵያ እርቀ ሰላም ኮሚሽን ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር “ዘላቂ መፍትሄ በሀገር በቀል የግጭት አፈታት ዘዴዎች” በሚል መሪ ሃሳብ የምክክር መድረክ እያካሄደ ነው።
በመድረኩ ከሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ 200 የሚጠጉ የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎችና ወጣቶች ተሳታፊዎች ናቸው።
መድረኩ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ወጣቶች ለሀገር ሰላም የበኩላቸውን እገዛ እንዲያደርጉ መዘጋጀቱም ተገልጿል።
በመድረኩ መክፈቻ ንግግር ያደረጉት ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነ እየሱስ ሱራፌል ኮሚሽኑ ከተቋቋመበት ጊዜ ጅምሮ የተለያዩ ተግበራትን ሲያከናውን መቆየቱን አንስተዋል።
የሌሎች አገራት ልምድ መቅሰም፣ ከክልል መስተዳደሮች ጋር ጥሩ የስራ ግንኙነት መፍጠር እና በክልሎች ቅርጫፍ መክፈት ኮሚሽኑ ያከናወናቸው ተግባራት መሆናቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል።
በኢትዮጵያ በርካታ ጥቃቶችና ግጭቶች መከሰታቸውን አስታውሰው፤ ኮሚሽኑ ሁሉንም አይነት ግጭቶች ብቻውን የመፍታት አቅም እንደሌለው አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ በባህላዊ መንገድ ግጭቶችን በመፍታት ረገድ የዳበረ ባህል ያላቸው ህዝቦች ባለቤት መሆኗም አንስተዋል።
በመሆኑም ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴን ለዘላቂ ሰላም መጠቀም ይገባል ነው ያሉት።
ኮሚሽኑ ከዚህ አንጻር የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችንና የሀገር ሽማግሌዎችን ያሳተፈ የግጭት አፈታት ስርዓት እንዲፈጠር እገዛ እያደረ መሆኑን ገልጸዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች በተለያዩ አከባቢዎች ከሚተገበሩ ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎች ላይ ልምድ እንዲቀስሙ እድል እንደሚፈጥርም ያላቸውን እምነት ተናግረዋል።
በሰላም ሚኒስቴር የሚኒስትር አማካሪና የብሔራዊ መግባባትና የማህበራዊ ሃብት ግንባታ ጀኔራል ዳይሬክተር ሚናስ ፍሰሃ በተወሰኑ ተቋማት ስራ ብቻ ዘላቂ ሰላም መረጋገጥ እንደማይችል ተናግረዋል።
በመሆኑም ሁሉም ዜጋ በሰላም ግንባታ ላይ የበኩሉን ሚና መወጣት አለበት ብለዋል።
የምክክር መድረኩ አንደኛው የሌላኛውን ችግር እንዲገነዘብ በማድረግ ለችግሮች የጋራ መፍትሔ እንዲፈጠር ሚናው የጎላ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ተሳታፊዎቹ በበኩላቸው መድረኩ የግጭቶች መነሻ ምን እንደሆነ ለመየትና መፍትሄ ለማስቀመጥ እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ሁሉም ዜጋ የበኩሉን ሚና እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።