ቀጥታ፡

በአዲስ አበባ በ2013 በጀት አመት 2 ሺህ 500 ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት በቁ

አዲስ አበባ  (ኢዜአ)  ሰኔ7/በ2013  በአዲስ አበባ በ2013 በጀት አመት 2 ሺህ 500 ፕሮጀክቶች ግንባታቸው ተጠናቆ ለአገልግሎት መብቃታቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ።፡

የከተማ አስተዳደሩ የኮንስትራክሽን ቢሮ በበጀት አመቱ የተሻለ አፈፃፀም ላስመዘገቡ ሰራተኞችና ድጋፍ ላደረጉ አካላት እውቅና ሰጥቷል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት እንዳሉት በ2013 በጀት አመት 2 ሺህ 500 ፕሮጀክቶች ግንባታቸውተጠናቆለአገልግሎት በቅተዋል።

ከፕሮጀክቶቹ መካከል 80 በመቶዎቹ አዲስ እንዲሁም 20 በመቶዎቹ በተለያዩ ምክንያቶች ግንባታቸው ሲጓተቱ የቆዩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የጤና ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች፣ የገበያ ማዕከላት ፣መንገዶችና የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች ከተከናወኑት ፕሮጀክቶች መካከል ተጠቃሾች መሆናቸውን ገልጸዋል።

ፕሮጀክቶቹ ለህዝቡ ያላቸው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ የጎላ እንደሆነ በመግለፅ ፤በቀጣይም ለህዝብ ጥቅም ከዚህ በላይ እንሰራለን ሲሉ አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያን እናበለፅጋታለን አዲስ አበባንም የኢትዮጵያ ተምሳሌት እናደርጋታለን ያሉት ምክትል ከንቲባዋ ለዚህም ስኬት የሁሉም ትብብርና ድጋፍ ያስፈልገናል ብለዋል።

አዲስ አበባን እንደስሟ አበባና ውብ እንዲሁም የቱሪስት መስህብ በማድረግ ገቢዋን ለማሳደግ እንሰራለንም ነው ያሉት።

የህዝብን የልማት ጥያቄ ለመመለስ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች፣ ሰራተኞችና ባለድርሻ አካላት ለሰሩት ስራም አመስግነዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ኮንስትራክሽን ቢሮ ሃላፊ ኢንጀነር አያልነሽ ሀብተማሪያም በበኩላቸው ቢሮው ፕሮጀክቶች በታቀደላቸው ጊዜና በጀት ግንባታቸው ተጠናቀው ለአገልግለት እንዲበቁ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

ለዚህ ስኬት የግንባታ ግብዓቶችን በፍጥነት በማቅረብና ብቃት ባላቸው ባለሙያዎች ግንባታቸው እንዲከናወን የክትትልና የድጋፍ ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል፡፡

ፕሮጀክቶቹ ልምድ የተገኘባቸውና የስራ ባህልን የሚያጎለብቱ እንደነበሩ ኢንጅነር አያልነሽ ተናግረዋል፡፡

ሁሉም ሰራተኞች፣ አመራሩና ድጋፍ ያደረጉ አካላትን በሰሩት ልክ እውቅና መስጠት ለቀጣይ የሚያበረታት በመሆኑ እውቅናና ሽልማት መሰጠቱን ገልፀዋል ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም