ቀጥታ፡

ምርጫው ሞጋች የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚፈጥር ተስፋ አለን - ጋዜጠኛ ንጉሴ አክሊሉ

ሰኔ 07 ቀን 2013 (ኢዜአ) "የስድስተኛውን ጠቅላላ ምርጫ ተከትሎ ሞጋችና የሃሳብ ፍጭት የሚታይበት ጠንካራ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚኖር ተስፋ አለን" ሲሉ አንጋፋው ጋዜጠኛ ንጉሴ አክሊሉ ተናገሩ።
በቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት የነበረው ምክር ቤት በሕዝብ ዘንድ ተሰሚነት ያላቸው፣ ሞጋችና የንጉሰ ነገሥቱን ውሳኔ የሚገዳደሩ አባላት እንደነበሩ ጋዜጠኛ ንጉሴ ያስታውሳሉ።

ለአብነትም የፊንጫ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታን የተጠየቀን 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የውጭ ብድር ሁለት ጊዜ ውድቅ በማድረግ ቀድሞ የጸደቀው ብድር በአግባቡ ጥቅም ላይ መዋሉን በማረጋገጥ እንዳጸደቀው ጠቅሰዋል።

በሌላ በኩል ፈላጭ ቆራጭ የነበሩ የጠቅላይ ግዛት አስተዳዳሪዎችን ሕዝባዊ በደል ሲያደርሱ የየአካባቢው ተወካዮች በሚያቀርቡት ጥያቄ አገረ ገዥዎች ይጠየቁ እንደነበርም ያወሳሉ።

የምክር ቤት አባላትም በምርጫ ወቅት ጠንካራ የምረጡኝ ቅስቀሳ ያደርጉ እንደነበር አስታውሰው፤ ተወካዮቹ በሕዝብ ዘንድ ተሰሚነት ያላቸውና ለአገር ተቆርቋሪ እንደነበሩ አመልክተዋል።

በምክር ቤቱ አባላት ዘንድ ሥርዓትና መከባበር እንደነበር ገልጸዋል።

በዘንድሮው አገራዊ ምርጫ ሂደት ለውጦች እንዳስተዋሉ ገልጸው፤ በእጩዎች መካከል መከባበር እንዳለ ማስተዋላቸውን ተናግረዋል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሞጋች ሃሳብ መጥፋቱን የገለጹት ጋዜጠኛ ንጉሴ፤ ከምርጫ 97 በስተቀር የይስሙላ ምርጫ ሲካሄድ እንደነበር መታዘባቸውን ገልጸዋል።

የዘንድሮው ምርጫ ዕጩዎችን በየጎዳናው የማስተዋወቅ እንቅስቃሴን በማድነቅ ፓርቲዎች ያቀረቧቸው ዕጩዎቹንም በሕዝብ የሚታወቁ፣ ተሰሚነት ያላቸውና በርካቶቹ በትምህርትም ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሱ ምሁራን መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

"ይህም የቀጣዩ ምክር ቤት አባላት ጠንካራና ሞጋች እንደሚሆኑ በበርካቶች ዘንድ ተስፋ አሳድሯል" የሚሉት ጋዜጠኛ ንጉሴ፤ አገሪቱ መልከ ብዙ ችግሮች ቢኖሩባትም ቀጣይ ግን ብዙ ተስፋ ሰጪ ነገሮች እንደሚኖሩት ገልጸዋል።

በቅድመ ምርጫ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች መንግሥት ጠንካራ ምክር ቤት ለማቋቋም ፍላጎት ማሳየቱን ገልጸው፤ 'የቀጣዩ ምክር ቤት ከወዲሁ ትልቅ ግምት ያሳደረ' እንደሆነ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም