ቀጥታ፡

በጉራጌ ዞን በደቡብ ሶዶ የብልጽግና ፓርቲ የድጋፍ ሰልፍ ተካሄደ

ሰኔ 7/2013 ( ኢዜአ) በጉራጌ ዞን በደቡብ ሶዶ የብልጽግና ፓርቲ የድጋፍ ሰልፍ ተካሄደ።

በብልጽግና ፓርቲ ሶዶን ወክለው ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚወዳደሩት የፌደሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ እጸገነት መንግሥቱ ባደረጉት ንግግር፤ ብልጽግና ፓርቲ ተስፋ ሰንቆ ወደ ብርሃን የሚጓዝ ባለ ብዙ ራእይ ፓርቲ ነው።

ፓርቲው የሥልጣኔ ትሩፋት የሚቋደስ፣ ለአፍሪካውያን ተምሳሌት የሚሆንና ለክብሩ የሚመጥን ኑሮ የሚኖር ሕዝብ ሊገነባ ቆርጦ መነሳቱንም ተናግረዋል።

ፓርቲው በትናንሽ ጉዳዮች ሳይጠመድ በሰፊው አቅዶ ለሀገር ብልፅግና የሚሰራ ፓርቲ መሆኑን በተግባር እንደሚያሳይ ጠቁመዋል።

ብልጽግና የጀመረው የለውጥ እርምጃ ለሚሊዮኖች መነቃቃት መፍጠሩንና በተለይም የወንድማማችነት ስሜት በመፍጠር ለብሔራዊ መግባባት በር መክፈቱን ገልጸዋል።

የአገሪቱ ኢኮኖሚ ከነበረበት ቁልቁለት ጉዞ ፈጥኖ እንዲወጣና ለኢኮኖሚው ዋስትና ተብለው የተጀመሩ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ከነበሩበት መጓተት ወጥተው እንዲጠናቀቁ መደረጉንም አንስተዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያው የውሃ ሙሌት ተጠናቆ ለሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት በቅድመ ዝግጅት ላይ አገሪቱ መገኘቷ ትልቅ ማሳያ ነው ብለዋል።

በፖለቲካው መስክም የተፈጠረውን የዴሞክራሲ ምህዳር የማስፋት ሥራ ትልቅ ለውጥ የታየበትና አበረታች ጅምር መሆኑን ምክትል አፈ ጉባኤዋ ጠቅሰዋል።

እነዚህና ሌሎችንም ለውጦችን በተደራራቢ ሰው ሰራሽና ተፈጥሮአዊ ችግሮች እያለፈ የመጣው ፓርቲው መላው ህዝቡ በተለይም የሶዶ ወረዳ ነዋሪ ብልጽግናን እንዲመርጥ ጠይቀዋል።

ኢትዮጵያ የአኩሪ ታሪኮች ባለቤት መሆኗን ገልጸው በዚህ አኩሪ ታሪክ ባላት አገር ላይ እጃቸውን የሚዘረጉ ሴረኞች እጃቸውን እንዲያነሱ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ተስማሚነትና ምዘና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር አቶ ተሻለ በልሁ ብልጽግና በኢኮኖሚው ዘርፍ ያመጣውን ለውጥ ይበልጥ በማጠናከርና በማጎልበት የህዝቡን ጥያቄዎች ለመፍታት ይሰራል ብለዋል።

በማህበራዊ፣ በፖለቲካ በተለይም በፍትህ ዘርፍ ሁሉም እኩል የሚሆንበትን ስርአት ለመገንባት እንደሚሰራም ጠቁመዋል።

የደቡብ ሶዶ አስተዳዳሪ አቶ መለሰ ጫካ በብልጽግና ወስጥ እንደ አገር የነበሩ የማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመፍታት የፓርቲው አባላት፣ ደጋፊዎችና አጠቃላይ ህዝቡ አስተዋጽኦው ከፍተኛ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ብልጽግና በአጭር አመታት ውስጥ ቆመው የነበሩ ሃሳቦችንና ፕሮጀክቶችን ማስቀጠልና ማጠናቀቅ መቻሉ ተግባርን መሰረት አድርጎ የሚሰራ ፓርቲ ለመሆኑ ማሳያ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም