የህዳሴ ግድብ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድጋፋችንን አጠናክረን እንቀጥላለን - የነገሌና የሰመራ-ሎግያ ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የህዳሴ ግድብ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድጋፋችንን አጠናክረን እንቀጥላለን - የነገሌና የሰመራ-ሎግያ ከተማ ነዋሪዎች
ነገሌ/ሰመራ ሀምሌ 27/2010 ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እስኪጠናቀቅ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የነገሌና የሰመራ-ሎግያ ከተማ ነዋሪዎች ገለጸ። የህዳሴው ግድብ ግንባታ ኘሮጀክት ዋና ስራ አስኪያጅ የነበሩት ኢንጅነር ስመኘው በቀለ ህይወት ቢያልፍም በአገሪቱ ህዝቦች የገንዘብና ባለሙያ አቅም የተጀመረው የግድቡ ግንባታ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የዜግነት ግዴታቸውን ይወጣሉ፡፡ በነገሌ ከተማ 03 ቀበሌ ነዋሪና የመንግስት ሰራተኛ አቶ መኮንን ገሺር በሰጡት አስተያየት በሀገሪቱ እየታየ ያለውን ለውጥና የህዳሴውን ግድብ ግንባታ ለማደናቀፍ የሚደረግ ሙከራ ተቀባይነት የለውም። ምንም እንኳ የኢንጅነሩ አሟሟት የሚያስቆጭ ቢሆንም ሀገሪቱ የበርካታ ባለሙያዎች መፍለቂያ በመሆኗ የግድቡ ግንባታ እንደማይሰጓጎል ገልጸዋል፡፡ እሳቸውም ለግድቡ ግንባታ የጀመሩትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡ አቶ መኮንን እንዳሉት እስካሁን በሁለት ዙር ደሞዛቸው የ8 ሺህ ብር ቦንድ ግዥ የፈጸሙ ሲሆን የግድቡ ግንባታ እስከሚጠናቀቅ ተሳትፎአቸውን አጠናክረው ይቀጥላሉ፡፡ ሌላው የከተማ ነዋሪና የኃይማኖት መሪ ሼህ ከድር አብዱረህማን በበኩላቸው ኢንጂነር ስመኘውን በመግደል የሚቆም ልማት እንደሌለ ገልፀዋል፡፡ በሀገሪቱ የተጀመረው የሰላምና የአንድነት ጉዞ ከዳር እንዲደርስ ምእመኑን በማስተማር፣ በመቀስቀስና በማስተባበር ኃላፊነታቸውን ለመወጣት መነሳሳታቸውን ተናግረዋል። በከተማ 01 ቀበሌ ነዋሪ አቶ ታደለ ''በኢንጂነሩ ሞት ተስፋ የምንቆርጥበት አንዳችም ምክንያት የለም'' ብለዋል። ''ይልቁንም ሁላችንም በአንድነትና በጋራ ተሰልፈን የጀመርነውን የህዳሴ ግድብ በማጠናቀቅ የጸረ ሰላም ኃይሎችን ሴራ ልናከሽፍ ይገባል'' ብለዋል። በተመሳሳይ ዜና ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ጫፍ እንዲደርስ የጀመሩትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በአፋር ክልል የሰመራ-ሎግያ ከተማ ነዋሪዎች ገልፀዋል፡፡ የሎግያ ከተማ ነዋሪ ወጣት ዘሃራ አብዱ እንደገለፀችው የህዳሴ ግድብ በራሳችን የገንዘብና የባለሙያ አቅም በመገንባት በሀገሪቱ አዲስ የልማት መነቃቃትና የተስፋ ብርሃን የታየበት ፕሮጀክት ነው፡፡ ይህን ኘሮጀክት ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ከግል ጥቅማቸውም ሆነ ከቤተሰባቸው አብልጠው ለሃገራቸውና ለህዝባቸው ያላቸውን ታማኝነት ያሳዩበትና በመጨረሻንም የሕይወት መስዋዕትንት የከፈሉበት መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ቢያልፉም የህዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደት በሚፈለገው ፍጥነት ተጠናቆ ለአገልግሎት አንዲበቃ በማድረግ ውለታቸውን ለመክፈል የቦንድ ግዥ ጨምሮ ማናቸውም አይነት ድጋፍ እንደምታደርግ ተናግራለች፡፡ የሰመራ ከተማ ነዋሪ አቶ ሁሴን ኡመር በበኩላቸው ለህዳሴ ግድብ ግንባታ በየአመቱ በወር ደሞዛቸው ቦንድ በመግዛት ድጋፋቸውን ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልፀዋል፡፡ በቀጣይም ኢንጂነር ስመኘው በቀለ የህይወት መስዋዕትነት የከፈሉበት የህዳሴ ግድብ እውን እንዲሆን የጀመሩትን ድጋፍ በበለጠ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡ የሎግያ ከተማ ነዋሪ አቶ ያሲን ኡመር የኢንጂነር ስመኘው ህልፈት ቢያሳዝንም የግድቡ ግንባታ አንዲጠናቀቅ በማድረግ ታሪኩ አብሮ እንዲታወስ አንደ አንድ ኢትዮጵዊ ኃላፊነት እንደሚወጡ አስታውቀዋል፡፡ የክልሉ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኡስማን ጠሃ የክልሉ ህብረተሰብ ባለፉት ሰባት አመታት ከ130 ሚሊዮን ብር በላይ ቦንድ ግዥና በስጦታ ድጋፍ ተደርጓል፡፡ በቀጣይም ኢንጂነር ስመኘሁ ጥሎብን ያለፈውን ሀገራዊ አደራ ለመወጣትና የግድቡ ግንባታ በተፋጠነ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ህብረተሰቡ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጠል ጠይቀዋል፡፡