ቀጥታ፡

በጉራጌ ዞን ሶዶ ወረዳ እና በዞኑ በምትገኘው ቡኢ ከተማ የብልጽግና ፓርቲ የድጋፍ ሰልፍ ተካሄደ

ሰኔ 6/2013 (ኢዜአ) በብልጽግና ፓርቲ ሶዶን ወክለው ለኅዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚወዳደሩት የፌደሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ እጸገነት መንግሥቱ ንግግር አድርገዋል።

ምክትል አፈ ጉባኤዋ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፤ ብልጽግና ፓርቲ ተስፋ ሰንቆ ወደ ብርሃን የሚጓዝ ባለ ብዙ ራእይ ፓርቲ ነው።

ፓርቲው የሥልጣኔ ትሩፋት የሚቋደስና ለአፍሪካውያን ተምሳሌት የሚሆንና ለክብሩ የሚመጥን ኑሮ የሚኖር ሕዝብ ሊገነባ ቆርጦ መነሳቱንም ተናግረዋል።

ፓርቲው በትናንሽ ጉዳዮች ሳይጠመድ በሰፊው አቅዶ ለሀገር ብልፅግና የሚሰራ ፓርቲ መሆኑን በተግባር እንደሚያሳይ ጠቁመዋል።

ብልጽግና የጀመረው የለውጥ እርምጃ ለሚሊዮኖች መነቃቃት መፍጠሩንና በተለይም የወንድማማችነት ስሜት በመፍጠር ለብሔራዊ መግባባት በር መክፈቱን ገልጸዋል።

የአገሪቱ ኢኮኖሚ ከነበረበት ቁልቁለት ጉዞ ፈጥኖ እንዲወጣና ለኢኮኖሚው ዋስትና ተብለው የተጀመሩ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ከነበሩበት መጓተት ወጥተው እንዲጠናቀቁ መደረጉንም አንስተዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያው የውሃ ሙሉት ተጠናቆ ለሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት በቅድመ ዝግጅት ላይ አገሪቱ መገኘቷ ትልቅ ማሳያ ነው ብለዋል።

በፖለቲካው መስክም የተፈጠረውን የዴሞክራሲ ምህዳር የማስፋት ሥራ ትልቅ ለውጥ የታየበትና አበራታች ጅምር መሆኑን ምክትል አፈ ጉባኤዋ ጠቅሰዋል እነዚህና ሌሎችንም ለውጦችን በተደራራቢ ሰው ሰራሽና ተፈጥሮአዊ ችግሮች እያለፈ ያመጣው ፓርቲው መላው ህዝቡ በተለይም የሶዶ ወረዳ ነዋሪ ብልጽግናን እንዲመርጥ ጠይቀዋል።

ኢትዮጰያ የአኩሪ ታሪኮች ባለቤት መሆኗን ገልጸው በዚህ አኩሪ ታሪክ ባላት አገር ላይ እጃቸውን የሚዘረጉ ሴረኞች እጃቸውን እንዲያነሱ አሳስበዋል።

በጉራጌ ዞን የብልጽግና ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ክፍሌ ለማ በበኩላቸው በለውጡ ኢትዮጵያ ከነበረችባቸው ውስብስብ ችግሮች እንድትወጣ በማኅበራዊ፣ በፖለቲካና በኢኮኖሚ ተጨባጭ ለውጦች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።

ለዚህም ሰሞኑን በተለያዩ የአገሪቱ አከባቢዎች እየተመረቁ ያሉት በርካታ ፕሮጀክቶች ማሳያ መሆናቸውን ጠቁመዋል። ፓርቲው በተለይም አገራዊ አንድነትን በማጠናከር ረገድ ትልቅ ስራ መስራቱን ገልጸዋል።

የሶዶ ወረዳ ዋና አስተዳደሪ አቶ በላይነህ ፋንታዬ፤ ኅዝቡ ከብልጽግና ፓርቲ ጋር አብሮ በመቆም እያሳየ ያለውን አብሮነት አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።በተለይም የታላቁ የህዳሴ ግድብ ሁለተኛ የውሃ ሙሌት በዘንደሮው ክረምት የሚካሄድ መሆኑን ገልጸው ለዚሁ ስኬት አገራዊ አንድነቱ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም