ቀጥታ፡

ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በስኬት መጠናቀቅ የህዝቡ አንድነት ይበልጥ መጠናከር አለበት…አቶ ታገሰ ጫፎ

አርባ ምንጭ፣ ሰኔ 05/201(ኢዜአ) የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሀ ሙሌትና ግንባታው በስኬት እንዲጠናቀቅ ህዝቡ ከጥንት የነበረውን አንድነት ይበልጥ ማጠናከር እንዳለበት አቶ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።
በአርባ ምንጭ ከተማ ለብልጽግና ፓርቲ የድጋፍ ሰልፍ ዛሬ ተደርጓል።

በሰልፉ ላይ የፓርቲው ከፍተኛ አመራርና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ እንደገለጹት ኢትዮጵያ በሁሉም የልማት መስኮች አንጸባራቂ ዉጤት እያስመዘገበች ትገኛለች።

የሃገር ህልውና እና የህዝቦች አብሮነት መገለጫ የሆነው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታና የሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት እንዲጠናቀቅ የህዝቡ አንድነት ከመቼውም ጊዜ በላይ መጠናከር እንዳለበት ተናግረዋል።

አካባቢውን ወክለው ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚወዳደሩት አቶ ታገሰ ሁለንተናዊ ዕድገትን በፍጥነት ለማረጋገጥና ህዝቡ በየደረጃዉ የልማቱ እኩል ተጠቃሚ እንዲሆን ፓርቲያቸው በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

ህዝቡ በሰፈር አጀንዳዎች ሳይከፋፈል የአገሪቱን አንድነት በማስጠበቅ ኢትዮጵያን ወደፊት ማስኬድ እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ ወደ ከፍታ ማማ በፍጥነት እየተጓዘች መሆኗን ያመለከቱት አቶ ታገሰ፤ የብልጽግና ፓርቲ ምልክት የሆነዉን አንፖልን እንዲመርጡ ለአባላትና ደጋፊዎች ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የአርባ ምጭ ከተማ ከንቲባ ሰብስቤ ቡናቤ በበኩላቸው “ብልጽግናን መምረጥ ለነገው ትውልድ የበለጸገች አገር ማውረስ ነው” ብለዋል፡፡

"በአርባ ምንጭ ከተማ በሁሉም መስክ ፈጣን ዕድገት እያስመዘገብን በመሆኑ ይሄንን የበለጠ ለማረጋገጥ ብልጽግና ፓርቲን መምረጥ ወሳኝ ነው" ሲሉም ተናግረዋል።

በአሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያ አንድነትና ሰላም በእጅጉ የሚያስፈልግበት ጊዜ በመሆኑ ይህን በማሳካቱ ረገድ ብልጽግና አስተማማኝ እንደሆነ የገለጸው ደግሞ የፓርቲው አባል የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪ ወጣት ቶማስ ማርቆስ ነው፡፡

ለሀገር ሰላምና ለህዝቦች አንድነት የሚጠበቅበትን ሀላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መሆኑንም ገልጿል።

የፌዴራል፣ የክልልና የዞን አመራሮች በተገኙበት የድጋፍ ሰልፍ ላይ አባላቱና ደጋፊዎች “ብልጽግ የአገር አለኝታ ነው”፣ “ብልጽግና ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እንዲጠናቀቅ ጠንክሮ ይሰራል” የሚሉ መልዕክቶችን አሰምተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም