ቀጥታ፡

በትግራይ ክልል ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ስልጠና እየተሰጠ ነው

መቀሌ፤ሰኔ 5/2013(ኢዜአ)በትግራይ ክልል የሚገኙ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ሥራቸውን በእውቀት እንዲደግፉና የበለጠ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የሚያስችል ስልጠና እየሰጠ መሆኑን የኢትዮጵያ ልማት ባንክ አስታወቀ፡፡

ባንኩ በትግራይ ለሚገኙ አነስተኛና መካካለኛ ኢንተርፕራይዞች ስልጠና እየሰጠ መሆኑን ዛሬ አስታውቋል፡፡

ስልጠናው ሀገሪቱ ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ እያደረገችው ለምትገኘው ጉዞ አጋዥ እንደሚሆንም ነው የተገለጸው፡፡

በኢትዮጵያ ልማት ባንክ የመቐለ ዲስትሪክት ሥራ አስኪያጅ አቶ ዮሐንስ አማረ ለኢዜአ እንዳሉት የስልጠናው ዋና ዓላማ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች በእውቀት የሚመራ ፕሮጀክት እንዲኖራቸው ማስቻል ነው፡፡

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከ2007 ጀምሮ ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ሲሰጥ የነበረውን የሊዝ ፋይናንሲንግ ሲገመግም የአንቀሳቃሾቹ በእውቀት አለመመራት ችግር እንዳለ መገንዘቡን አስታውሰዋል።

"በመቐለ እየተሰጠ የሚገኘው ስልጠናም አንቀሳቃሾች ሥራቸውን በእውቀት እንዲፈትሹና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ባለሃብቶች የቢዝነስ ዝግጅት እውቀትንና የሰው ሃይላቸውንም እንዴት ማደራጀት እንዳለባቸው ዕውቀት የሚያገኙበት ስልጠና መሆኑንም ነው ያስረዱት።

በተጨማሪም አንቀሳቃሾች ፋይናንሳቸውን ለማስተዳደር እውቀት የሚያገኙበት መሆኑን የገለጹት ሥራ አስኪያጁ፣ የገበያ ትስስር ጉዳይም ትኩረት እንደተደረገበት አመልክተዋል፡፡

አቶ ዮሐንስ እንዳሉት ስልጠናው ወደ መሬት ወርዶ የሚፈለገውን ውጤት እንዲያስመዘግብ ልማት ባንክ በቁርጠኝነት ይሰራል።

አነስተኛና መካከለኛ አንቀሳቃሾችም ከስልጠናው ያገኙትን እውቀት በመጠቀም በሥራቸው ላይ ለውጥ ሊያመጡ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በመቐለ እየተሰጠ በሚገኘው ስልጠና ከ300 በላይ የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ፡፡

በልማት ባንክ እየተሰጠ የሚገኘው ስልጠናም በሀገር አቀፍ ደረጃ በ12 ማዕከላት በተመሳሳይ እየተሰጠ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም