ከሐዋላ የባንክ አገልግሎት 2 ነጥብ 4 ቢሊዮን የሚጠጋ ዶላር ወደ ሀገር ቤት ገብቷል - ኢዜአ አማርኛ
ከሐዋላ የባንክ አገልግሎት 2 ነጥብ 4 ቢሊዮን የሚጠጋ ዶላር ወደ ሀገር ቤት ገብቷል
ሰኔ 5 ቀን 2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከሐዋላ የባንክ አገልግሎት 2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ በባንኩ በኩል ወደ ሀገር ውስጥ መግባቱን አስታወቀ፡፡
ባንኩ በየዓመቱ በፈረንጆቹ ሰኔ የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የቤተሰብ የሐዋላ ቀን አስመልክቶ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።
የባንኩ የሐዋላ አገልግሎት ሥራ አስኪያጅ አቶ ዮሐንስ ሊቁ እንዳሉት ከሀገር ውጭ ያሉ ኢትዮጵያዊያንና ትውልድ ኢትዮጵዊያን ለቤተሰቦቻቸው የሚልኩት ገንዘብ ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ እድገት ያለው አስተዋጽኦው የጎላ ነው፡፡
በተያዘው ዓመት ያለፉት ዘጠኝ ወራት ከነዚሁ ዜጎች 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዶላር በባንኩ በኩል ወደሀገር ውስጥ መግባቱንም ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ከፍተኛ የገንዘብ መጠን በጥቁር ገበያ በኩል እንደሚልፍም ነው የጠቆሙት፡፡
"ጥቁር ገበያው የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሬ ግኝትን በመጉዳት ባንኩ ሀገራዊ ልማቶችን ለመደገፍ በሚያደርገው ጥረት ላይ አሉታዊ ጫና ያሳድራል" ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የመሃል ሪጅን ሥራ አስኪያጅ አቶ ኪዳኔ መንገሻ በበኩላቸው እንዳሉት፣ በኢትዮጵያ የሚካሄዱ እንደ ሕዳሴ ግድብ ያሉ ትላልቅ ፕሮጀክቶች በገንዘብ የሚደገፉት በባንኮች በኩል በሚገባ የውጭ ምንዛሬ ነው።
"በሐዋላ መልክ ለታዳጊ ሀገራት የሚላከው የገንዘብ መጠን ከዓለም ማቀፍ ለጋሾች ከሚገኘው የልማት እርዳታ በሦስት እጥፍ እንደሚበልጥ ጥናቶች ያመላክታሉ" ያሉት አቶ ኪዳኔ፣ ኢትጵዮጵያም የዚህ ተጠቃሚ እንደሆነች ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም በውጭ ሀገራት የሚገኙ ዜጎች ለቤተሰቦቻቸው ገንዘብ ሲልኩ በባንኮች በኩል ቢልኩና ተቀባዮችም በባንክ በኩል ቢመነዝሩ ጎን ለጎን ሀገር እየደገፉ መሆኑን ጭምር ማስተማርና ማስገንዘብ እንደሚገባ አብራርተዋል፡፡
አቶ ኪዳኔ እንዳሉት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ትላልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን በገንዘብ ለመደገፍ ለሚያደርገው እንቅስቃሴ በሐዋላ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ገንዘቦች ጠቀሜታቸው የጎላ ነው።
በመሆኑም ከውጪ የሚላኩ ገንዘቦች የባንክ ስርአቱን ጠብቀው ቢገቡ ለሀገራዊ ልማት የሚኖራቸው ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኢንተርናሽናል ባንኪንግ ክፍል የኤክስፖርትና ኢንካሚንግ ዳይሬክተር አቶ ጌቱ ብሩ ከሐዋላ የሚገኘውን የገንዘብ መጠን ለማሳደግና የጥቁር ገበያውን ለማዳከም ባንኩ ወደ ህብረተሰቡ ተደራሽ በመሆን እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ባለፉት ሰባት ዓመታት ይህንኑ ዘርፍ ለመደገፍ በዘረጋው "ይቆጥቡ ይሸለሙ መርሃ ግብር" ከ46 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ ለሽልማት ማቅረቡን አስታውሰዋል።
ሌሎች የህብረተሰቡን ግንዛቤ የሚያሳድጉ ሥራዎችን እየሰራ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
በተባበሩት መንግስታት ዘላቂ የልማት ግብች ትግበራ ላይ በሐዋላ መልክ ለድሃ ሀገሮች የሚላከው ገንዘብ ትልቅ ስፍራ ተሰጥቶታል።
ትንበያዎች እንደሚያሳዩት እ.አ.አ ከ2015 እስከ 2030 ባለው የዘላቂ ግቦች ትግበራ ወቅት አንድ ቢሊዮን ሰዎች በገንዘብ ላኪነትና ተቀባይነት ይሳተፋሉ።
በዚህም 8 ነጥብ 5 ትሪሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወደታዳጊ አገሮች እንደሚላክ ይጠበቃል።
እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር ከ2015 ጀምሮ በየዓመቱ እየተከበረ ያለው ዓለም አቀፍ የቤተሰብ የሐዋላ ቀን በመጪው ረቡዕ በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር ከባንኩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡