የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ የልጆች ቻናል ከፈተ - ኢዜአ አማርኛ
የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ የልጆች ቻናል ከፈተ
አዳማ ፤ ሰኔ 5ቀን 2013 (ኢዜአ) የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ "ጋሜ " የተሰኘ የልጆች ቻናል በመክፈት ዛሬ አገልግሎት መሰጠት ጀመረ።
ቻናሉን መርቀው ስራ ያስጀመሩት የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ እንዳሉት፤ "ጋሜ " የልጆች ቻናል በገዳ ስርዓት ወስጥ ታዳጊዎች በስነ-ምግባር ተኮትኩተው እንዲያድጉ ለማስቻል የተመቻቸ ነው።
በተለይ የነገ ሀገር ተረካቢ ታዳጊዎች ባህላቸውን፣ ታሪካቸውንና ማንነታቸውን አውቀው እንዲያድጉ ቻናሉ የላቀ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል።
የተቋሙ ሠራተኞች ሌተ ተቀን ሠርተው ኦቢኤን ዛሬ ለደረሰበት ደረጃ ማብቃታቸውን ጠቅሰው አሁን በ17 ቋንቋዎች በማሰራጨትና የብዙሃን ልሳን በመሆን በሀገሪቷ ቀዳሚ ነው ብለዋል።የኦቢኤን የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አዲሱ አረጋ በበኩላቸው፤ ኦቢኤን ከአንድ ቻናል በመነሳት ዛሬ ላይ ሶስተኛ ቻናል ላይ መድረሱን ተናግረዋል።
ተቋሙ የትውልድ ልሳን መሆን ችሏል ያሉት አቶ አዲሱ ፤ ቻናሉ የልጆች መማማሪያ መሆኑን አስረድተዋል።ይህ "ጋሜ" የተሰኘው ቻናል ሁለት ዘመናዊ ስቱዲዮዎች ያሉት መሆኑን ያስታወቁት ደግሞ የኦቢኤን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዝናቡ አስራት ናቸው።
በአሁኑ ጊዜ ኦቢኤን በ14 የሀገር ውስጥና በሶስት የውጭ ቋንቋዎች እያሰራጨ እንደሚገኝ ያመለከቱት አቶ ዝናቡ ፤ በዚህም የብሔር ብሔረሰቦች ልሳንና ድምፅ ላጡ ድምፅ መሆኑን በተግባር ያረጋገጠና በቅርቡ በቻይንኛና ፈረንሳይኛ ቋንቋዎች ስርጭት ይጀምራል ብለዋል።
ኦቢን ዛሬ ለደረሰበት ደረጃ የክልሉ መንግስትና የለውጡ አመራሮች ሚና የላቀ መሆኑን ጠቅሰዋል።ተቋሙ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በነበረው ወቅታዊ የፀጥታ ችግር ለተጎዱ ዜጎች 15 ሚሊዮን ብር የሚገመት እህል ድጋፍ ማድረጉንም አስታውሰዋል።
የህዝብ ልሳንና ድምፅ ሆኖ የጀመራቸውን ተግባራት አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እና የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ ዛሬ አብሮ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል።
በሁለቱ ተቋማት መካከል የመግባቢያ ሰነዱ መፈረሙ ያላቸውን ልምድ በመለዋወጥ በጋራ ለመስራት የሚያስችል መሆኑ ተመልክቷል።
የመግባቢያ ሰነዱ የተፈራረሙት በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ እና የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዝናቡ አስራት ናቸው።
በምረቃው ስነ ስርዓት የፌደራልና ክልል አመራሮች ተገኝተዋል።