በትግራይ ክልል በተጀመረው የኮሌራ በሽታ መከላከያ ክትባት ሁለት ሚሊዮን ዜጎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በትግራይ ክልል በተጀመረው የኮሌራ በሽታ መከላከያ ክትባት ሁለት ሚሊዮን ዜጎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተገለጸ
መቀሌ፤ ሰኔ 05/2013 (ኢዜአ) በትግራይ ክልል በጀመረው የኮሌራ በሽታ መከላከያ ክትባት በ13 ወረዳዎች የሚገኙ ሁለት ሚሊዮን ዜጎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ጤና ቢሮ ገለጸ።
ክትባቱ የተጀመረው ዛሬ በመቀሌ ከተማ ሓድነት ክፍለ ከተማ ማይወይኒ ትምህርት ቤት በሚገኙ ተፈናቃዮች አገልግሎቱን በመስጠት ነው ።
የጤና ቢሮው ሃላፊ ዶክተር ፋሲካ ዓምደስላሴ በዚህ ወቅት ላይ እንዳሉት፣ ክትባቱ የሚሰጠው ተፈናቃዮች በሚገኙባቸው ጊዜያዊ መጠለያዎች ውስጥ እና በክልሉ ወረዳዎች ለሚገኙ ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ነው።
በዘመቻ በሚሰጠው የኮሌራ በሽታ መከላከያ ክትባት በክልሉ የሚገኙ ሁለት ሚሊዮን ዜጎች ተጠቃሚ ይሆናሉ ብለዋል።
የክትባት ዘመቻውን ለማሳካት በሚደረገው እንቅስቃሴ በመሳተፍ ሁሉም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የተጣለባቸውን ሃላፊነት እንዲወጡ ዶክተር ፋሲካ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አስቻለው አባይነህ በበኩላቸው፣ በትግራይ ክልል የተጀመረው የኮሌራ ክትባት ዘመቻ ለማሳካት የሚያስችሉ የተለያዩ ድጋፎች መደረጋቸውን ገልጸዋል።
በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች በተመረጡ ስድስት ክልሎች ህብረተሰቡ በኮሌራ በሽታ እንዳይጠቃ አስቀድሞ ለመከላከል ቀደም ሲል የክትባት ዘመቻው ሲካሄድ መቆየቱንና ውጤታማ መሆኑን ዶክተር አስቻለው አስታውቀዋል።
የክትባት ዘመቻውን ለማሳካት የሚያስችሉ መድሃኒቶች፤ የጤና ባለሙያዎችና ሌሎችንም ቁሳቁሶች ድጋፍ እያደረጉ ላሉ ድርጅቶች ዶክተር አስቻለው ምስጋና አቅርበዋል።
በዓለም ጤና ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ ዶክተር ቦሬማ ሶምሞ እንዳሉት፤ በትግራይ ዛሬ የተጀመረው የኮሌራ በሽታ መከላከያ ክትባት ዘመቻ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም ቀደም ሲልም በሽታው የመከሰት እድል ስለነበረበት የክትባት ዘመቻው አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
በትግይ ክልል እስከ ሰኔ 7/2013 ዓ.ም. የሚቆየውን የክትባት ዘመቻው ዛሬ ያስጀመሩት ዶክተር ፋሲካ ዓምደስላሴ ፣ ዶክተር አስቻለው አባይነህ እና በዓለም ጤና ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ ዶክተር ቦሬማ ሶምሞ በጋራ በመሆን ነው።