ቀጥታ፡

የመንግስትን የሰላም አማራጭ ለተቀበሉ ከአንድ ሺህ በላይ ታጣቂዎች ሁለተኛ ዙር የተሃድሶ ስልጠና መስጠት ተጀመረ

ሰኔ 5/ 2013 ( ኢዜአ) በመተከል ዞን በጫካ ሲንቀሳቀሱ ለነበሩና የመንግስትን የሰላም ጥሪ አማራጭ ለተቀበሉ ከአንድ ሺህ 600 በላይ ታጣቂዎች ሁለተኛ ዙር የተሃድሶ ስልጠና መስጠት ተጀመረ።

ስልጠናው የተጀመረው የመተከል ዞን የተቀናጀ ግብረ ሃይል ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ሌተናል ጄኔራል አስራት ዴኔሮ፣ የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ከፍተኛ አመራሮች፣ የዞኑና የወረዳ የሥራ ኃላፊዎች እና የጸጥታ አካላት ከፍተኛ መኮንኖች በተገኙበት ነው።

በጫካ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ አካላት ከስልጠናው በኋላ የሰላምና የልማት ኃይል ሆነው እንዲወጡ የሚያስችል የተሃድሶ ስልጠና እንደሚሰጣቸው ተገልጿል።

በዞኑ ተፈጥረው በነበሩ ችግሮች ምክንያት 43 ትልልቅ የልማት ፕሮጀክቶች ባለፉት ሦስት ዓመታት ሳይሰሩ መቅረታቸው ተመላክቷል።

በዚህም በፕሮጀክቶቹ ለበርካታ ወጣቶች ይፈጠር የነበረውን የሥራ እድል ማሳካት እንዳልተቻለ ነው የተገለጸው።

ቀጣይ በዞኑ ያለውን የተፈጥሮ ሃብት ለማልማትና የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ወደ ሥራ ለማስገባት ሁሉም ዜጋ ለሰላም ዘብና ምሳሌ ሆኖ መስራት አለበት ተብሏል።

በአሁኑ ወቅት በዞኑ የመጣውን አንጻራዊ ሰላም ዘላቂ ለማድረግ ማንኛውም ዜጋ ለሰላም መስራት እንዳለበትም ነው የተጠቆመው።

የመተከል ዞን የተቀናጀ ግብረ ሃይል ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ሌተናል ጄኔራል አስራት ዴኔሮ፤ መተከል ትታወቅበት ከነበረው አብሮነት ወጥታ አለመረጋጋት መፈጠሩ በርካታ ኢትዮጵያዊያንን ያሳዘነ እንደነበር ገልጸዋል።

"የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብሎ በጫካ መንቀሳቀስን በመተው ለሰላም ተሃድሶ ስልጠና መምጣት  ከየትኛውም አማራጭ ሁሉ የተሻለ ነው" ብለዋል።

መንግስትና ሰልጣኞች ሊግባቡበት የሚያስችል መድረክ መኖር አለበት በሚል የተሃድሶ ስልጠናው መዘጋጀቱን አስረድተዋል።

እያንዳንዱ የሰላም ሰልጣኝ ኃላፊነቱን አውቆ ለሰላም ዘብ እንዲሆን በማሰብ የተዘጋጀ መሆኑንም ነው ሌተናል ጄኔራል አስራት ዴኔሮ ያመለከቱት።

የሰላም ሰልጣኞችን መልሶ ለማቋቋም የመግባቢያ ሰነድ ከመፈራረም ባለፈ የተለያዩ ባለሙያዎችን ያቀፈና ራሱን የቻለ ጽህፈት ቤት ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ብልጽግና ፓርቲ አደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ መንግስቱ ቴሶ፣ ስልጠናው ለዘላቂ ሰላም መጎልበት ሰልጣኞች ድርሻቸውን እንዲወስዱ ግንዛቤ የመፍጠር ዋነኛ ዓላማ እንዳለውም ገልጸዋል።

ተሳታፊዎች ወደ ስልጠና የገቡት የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው በመምጣታቸው መሆኑንም ጠቁመዋል።ተሃድሶ ሰልጣኝ ወጣቶች አገርን ለማልማትና ለመለወጥ ያላቸውን እምቅ አቅም ተጠቅመው ህዝቡን በሰላምና ልማት መካስ እንዳለባቸው ያስገነዘቡት ደግሞ የሰባተኛ መካናይዝድ ክፍለ ጦር ዋና አዛዥ ኮሎኔል በስፋት ፋንታዬ ናቸው።

ወጣቶቹ የማይጠቅማቸውን በመተው ቀጣይ በሚከናወኑ የልማት ሥራዎች ላይ የሰላም አውራ፣ ምሳሌና ግንባር ቀደም ተሰላፊ በመሆን ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ጋር እንዲሰሩ አስገንዝበዋል።

"መንግስት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ ተጠራጥረው አሁንም በጫካ ለሚንቀሳቀሱ አካላት ከሰላም የሚገኘውን ዋጋ በማስረዳት ወደ ሰላማዊ ህይወት እንዲመለሱ ማድረግ ይገባቸዋል" ብለዋል።ስልጠናው ህገ መንግስትና ህብረብሔራዊ ወንድማማችነት፣ አገራዊ ለውጥና የጉምዝ ህዝብ ጥያቄ፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ እና የስነ-ልቦና ዝግጁነት በሚሉ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ ይሰጣል።  

በተጨማሪም የወንጀል መከላከልና በጎ ስነ-ምግባር፣ ብሔራዊ ደህንነት፣ የትጥቅ አያያዝና አስተዳደር እንዲሁም የጉምዝ ህዝብ እሴት፣ መስተጋብርና ግጭት አፈታት በሚሉት ርዕሰ ጉዳዮች ላይ እንደሚሰጥ ለማወቅ ተችሏል።

ከዚህ በፊት 500 ታጣቂዎች በአንደኛ ዙር የተሀድሶ ስልጠና የወሰዱ ሲሆን ከእነዚህ መካከል ብዙዎቹ አመራር እንደነበሩ መረጃዎች ያሳያሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም