ቀጥታ፡

የማንቡክ ከተማ ነዋሪዎች የተፈጠረውን አንጻራዊ ሰላም በዘላቂነት ለማስቀጠል በጋራ እንደሚሰሩ ገለጹ

ሰኔ 5 /2013 (ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ መተከል ዞኑ የተፈጠረውን አንጻራዊ ሰላም በዘላቂነት ለማስቀጠል በጋራ እንደሚሰሩ በዳንጉር ወረዳ የማንቡክ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።

የዞኑን ሰላም ለመመለስ የተቀናጀ ግብረ ሃይል ኮማንድ ፖስት አቋቁሞ ባከናወናቸው ተግባራት አንጻራዊ ሰላም ለማስፈን ተችሏል፡፡

የኢዜአ ሪፖርተር በዳንጉር ወረዳ ማምቡክ ከተማ የተለያዩ አካባቢዎች ያለውን የሰላም ሁኔታ በመቃት የማህበረሰቡ እንቅስቃሴ ወደነበረበት ሁኔታ እየተመለሰ ስለመሆኑ ታዝቧል።

ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት ሲሄዱ፣ ሱቆች አገልግሎት ሲሰጡ፣ ባንክና ሌሎች የመንግስት ተቋማት ተከፍተው መደበኛ ስራዎቻቸውን ማከናወን ጀምረዋል።

በማምቡክ ወረዳ ክትሌ ቀበሌ በሸቀጣሸቀጥ ንግድ ሥራ የተሰማራው ወጣት ፈቃዱ አስረስ እንዳለው፤ ከተማዋ ከነበረችበት የሰላም እጦት በመውጣቷ የተሻለ ሰላም እየታየባት ነው።

"በቀጣይም አርሶ አደሩ ወደ እርሻ ሥራው ተመልሶ መደበኛ ተግባሩን እንዲያከናውን ቢደረግ የበለጠ ለውጥ ሊመጣ ይችላል" ሲልም እምነቱን ገልጿል።

አቶ ጥላሁን ጀምበሬ በበኩላቸው ቀደም ሲል በተፈጠረው የሰላም እጦት ምክንያት ነዋሪዎች ከቀዬአቸው ተፈናቅለውና ወደጫካ ገብተው እንደነበር አስታውሰው፤ በአሁኑ ወቅት ሰላማዊ እንቅስቃሴ መፈጠሩን ገልጸዋል።

የጸጥታው ሁኔታ እየተሻሻለ በመምጣቱ ለንግድ ሥራው ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረ መሆኑን የገለጸው ደግሞ በማምቡክ ከተማ በሸቀጣሸቀጥ ንግድ ሥራ የተሰማራው ሌላኛው ወጣት ተመስገን ሞላ ነው።

ወጣት በቀለ አደሜ የሰላም መደፍረስ በነበረባቸው ጊዜያት በነጻነት ለመንቀሳቀስ ችግር እንደነበር አስታውሶ፣ በአሁኑ ወቅት የንግድና ሌሎች እንቅስቃሴዎች እየተሻሻሉ መምጣታቸውን ጠቁሟል።

አስተያየት ሰጪዎቹ መንግስት በአካባቢው ሰላም ለማስጠበቅ የአገር መከላከያ ሠራዊትና ሌሎች የጸጥታ አካላትን አሰማርቶ እየወሰደ ያለው እርምጃ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

የዞኑ የተቀናጀ ግብረ ሃይል ኮማንድ ፖስት እያከናወናቸው ባሉ ተግባራትም ምስጋና ሊቸራቸው እንደሚገባ ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት የተፈጠረውን አንጻራዊ ሰላም በዘላቂነት ለማስቀጠል ህብረተሰቡ ከጸጥታ ኃይል ጋር ተቀራርቦ በመስራት ወደ ልማት ሥራዎች መግባት እንዳለበት ተናግረዋል።

በቀጣይም ነባር አብሮ የመኖር ባህሉን በማጠናከር የቀደመ አንድነቱን ማስቀጠል እንዳለበት ነው የገለጹት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም